ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም ድረስ ቀጥሏል

ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ በመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ እልባትን እንዳገኘ ቢገልጽም ተቃውሞ አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ከተቃውሞው ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱና በየከተሞቹ ያሉ የጸጥታ ሃይሎች ከአካባቢው እንዲወጡ የሚጠይቁ ተቃውሞዎች በምስራቅ ሃረርጌና በተለያዩ የክልል ከተሞች እየተካሄዱ መሆኑም ታውቋል።

አራተኛ ወሩን ዘልቆ የከሚገኘው ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ2ሺ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻን ጭምር በማካሄድ ነዋሪዎችን እያሰሩ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ የመንግስት ተወካዮችም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክርን እያካሄዱ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።