ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ 5ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች እንደታሰሩ ታወቀ

ኢሳት ዜና (ታህሳስ 18 ፣ 2008)

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ቀጥሎ በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች የተያዙ ሰዎች ቁጥር አራት ሺ አካባቢ መድረሱን የኦሮሚያ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሰኞ አስታወቀ።

ለእስር ከተዳረጉት መካከልም 500 ያህሉ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሎዎች የሚገኙ አባላት መሆናቸዉን የኦፌኮ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ በቀለ ነገአ ለሀገር ዉስጥ መገናኛ ገልጸዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ ሁለት የስራ አስፈጻሚዎቹ እና ስድስት የወጣት ሊግ አመራሮች የታሰሩበት ኦፌኮ በቅረቡ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀስቀሰዉ ተቃዉሞ ለታሰሩት ሰዎችና የፓርቲዉ አባላት እንግልት ምክንያት መሆኑን አስታዉቋል።

የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት የሀይል እርምጃም ከፍተኛና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥርም 1ሺ 500 አካባቢ መድረሱን አቶ በቀለ ገልጻዋል።

ከአዲስ አበባ ማሰተር ፕላን ጋር በተናኘ የተቀሰቀስዉን ተቃዉሞ እልባት ለመስጠትም መንግስት የሚጠቅመዉ ጠብመንጃ አንስቶ ንጹሀንን መግደል ሳይሆን ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት እንደሆነ የኦፌኮ አመራር አክለው ተናግረዋል።

ሒዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ግድያዉን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት የከፈተዉ የእስር ዘመቻም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታዉቋል።

የሟቾችንም ሆነ ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቦ የሚገኘው መንግስት ሁከትና ብጥብጥን ቀስቅሰዋል ባላቸዉ አካላት ላይ የሚወስደዉን እርምጃ አጠናክሮ እንድሚቀጥል በመግለጽ ላይ ይገኛል።

ሰሞኑን የመንግስት ባለስልጣናት የሰጡት ይህንኑ ዛቻ ተከትሎም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የፓረቲ አባላትና ደጋፊዎች እየታሰሩ እንደሚገኙም ታዉቋል።

ከኦፌኮ በተጨማሪ ሰማያዊ ፓርቲ በርካታ አባላቱ ለእስር እየተዳረጉበትና እንግልት እየደረሰባቸዉ እንደሆነም ሰኞ አመልክቷል።

የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ የተጎጂ ሰዎችን ቁጥር መግለጽ ያልፈለገው፣ ጉዳዩ ምረመራ እየተካሄድበት እንደሚገኝ በመሆኑ ነው ብሏል።

አሜርካንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላማዊ ስልፍ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ የሚወስደዉን እርምጃ እንዲያቆም አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰዉን ተቃዉሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆነዉ የአዉሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከመንግስት ጋር ልዩ ምክክር ማካሄዳቸዉ ተገልጿል።

ከመንግስት ተወካዮች ጋር ምክክር ያካሄድዉ ህብረቱ ለተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ ሁለገብ ዉይይት እንዲካሄድና የህግ የበላይነት እንዲከበር ጠይቋል።

የህብረቱ አባላት ከመንግስት ተወካዮች ጋር ከመመካከራቸዉ አስቀድሞ የተናጠል ዉይይትን እንዳካሄዱም ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የእዉሮፓ ህብረት ከዋና መቀመጫው ብራስልስ ሰሞኑን ባወጣው መገለጫ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ ሰላማዊ መፍትሔን እንዲሰጥ መጠየቁንም ይታወሳል።