ኢሳት (ኅዳር 22 ፥ 2009)
አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ውስጥ ከሚኒስትር ጀምሮ እስከታችኛው ዕርከን የሚሰሩ በሙሉ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አገልጋዮች መሆናቸውን በጀርመን ፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደርባ የነበሩ ገለጹ። ከስርዓቱ ጋር በመቆየታቸው መጸጸታቸውንም የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀው ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ለለውጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
በጀርመን ፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ማዕረግ የዳያስፖራ ዘርፍ ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትና በቅርቡ ከስርዓቱ የተለዩት አቶ ግርማ መንገሻ ይህንን የገለጹት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው። በኦህዴድ አባልነት ስርዓቱ ተቀላቅለው ለደረሱበት ሃላፊነት መብቃታቸውንም አስረድተዋል።
በቆንስላው ውስጥ ከሚሰሩት የኢምባሲው ሰራተኞች አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ግርማ መንገሻ፣ በፍራንክፈርት ከተማ ከሚገኙ የስርዓቱ ደጋፊዎች 90% የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውም አስረድተዋል። የቀሩትም 10 በመቶ የሚሆኑት ከተለያዩ ብሄረሰብ ቢሆኑም፣ እነዚህ በሃገር ቤት ንብረትና ንግድ ያላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል። ከመካከላቸው 1 በመቶ የሚሆኑት በቅንነት ሃገራቸውን እያሰቡ ከኢምባሲው ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ መሆናቸው ገልጸዋል።
በዲያስፖራው ክፍል ሃላፊነታቸው ቁጥሮችን በማጋነንና በማዛባት ሪፖርት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን፣ ይህም የተለመደና በሃላፊዎች የሚደገፍ አሰራር እንደነበርም አብራርተዋል። በዲያስፖራ የብሄረሰብ ልማት ድርጅቶችን ለማቋቋም የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን፣ በደቡብ በኩል የልማት ማህበር ተብሎ የተቋቋመ ቢኖርም፣ አባላቱ ራሳቸው አመራሮቹ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል። የትግራይ ልማት ማህበር ግን ቀደም ሲልም የነበረ መሆኑን አብራርተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ዓመጽ በተቀጣጠለው ወቅት ዓመጹን ተቆጣጥረዋል የሚል መግለጫ እንዲሰጥ ተዘጋጅቶ ነበር ያሉት አቶ ግርማ መንገሻ፣ የሟቾቹን ቁጥር እንዳንናገር እንከለከል ነበር ሲሉም አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ይዞታ ላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰጡት መግለጫ እንዲለዝብ ስራ ይሰጠን ነበር ያሉት አቶ ግርማ መንገሻ፣ ሰብዓዊ መብት አለመርገጥ እየተቻለ፣ ሪፖርቱ መደበቁ እንዳማይገባቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በስርዓቱ ውስጥ ከትግራይ ተወላጆች ውጭ ያሉ ከሚኒስትር እስከ ተራ ሰራተኛ ሚናቸው አገልጋይነት መሆኑንም በመዘርዘር ስልጣን በህወሃት ሰዎች እጅ መሆኑን አስረድተዋል።