ከሚኒስትርነት ወርደው በአምባሳደርነት መሾማቸውን አያውቁም ነበር ተባለ

( አስር )ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-የማዕድን ሚኒስትር በመሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት ያገለገሉትት ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ሲሾሙ ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ከ16 ዓመታት በላይ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውስጥ ከኤክስፐርትነት እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ባሉት የሀላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ የቆዩትና እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 2010 የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተለያየ አደረጃጀት ይዞ ለሁለት ሲከፈል የማዕድን ሚኒስትር በመሆን በአቶ መለስ ዜናዊ አቅራቢነት የተሾሙት የኦህዴድ አባሏ ወ/ሮ ስንቅነሽ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ሳይነገር ከአማራው ክልል ፕሬዚደንት አቶ አያሌው ጎበዜ ጋር ባለሙሉ አምባሳደር በመሆን በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ምንጮቻችን እንደተናገሩት ወ/ሮ ስንቅነሽ በአቅም ችግር ከዚህ ቀደም የተገመገሙ ሲሆን ከሃላፊነታቸው ሲነሱ እንደማንኛውም ሰው በራዲዮና በቴሌቪዥን ከመስማታቸው ውጪ በቀጥታ የተነገራቸው ነገር አልነበረም፡፡

ወ/ሮ ስንቅነሽ የአዳሚ ቱሉ የኬሚካል ድርጅትና የኢትዮጽያ ማዕድን ልማት ድርጅትን በቦርድ ሰብሳቢነት፣የመንገዶች ባለስልጣን፣የኢትዮጽያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ፣የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልም ነበሩ፡፡

ወ/ሮ ስንቅነሽ ግልጽነት ከጎደለው የጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔ በይፋ ከተነሱ ሴት ሚኒስትሮች መካከል ከወ/ሮ አስቴር ማሞ የቀጠሉ ናቸው፡፡