ከመቀሌ አቻው ጋር ጨዋታ ያደረገው የባህር ዳር ከነማ ክለብ ጥፋተኛ ተብሎ ቅጣት ተፈረደበት

ኢሳት (ግንቦት 17 ፥ 2009)

ከመቀሌ አቻው ጋር ሲጫወት በመቀሌ ደጋፊዎች ተደብድቦ ወደ አማራ ክልል የተመለሰው የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥፋተኛ ተብሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት ተጣለበት።

የባህር ዳር ከነማ ክለብ በረኛን ጨምሮ 4 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ተባርረው በ7ቱ ብቻ ወደ መቀሌ ሄዶ ደጋፊ በሌለበት ዝግ ስታዲየም ጨዋታው ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለው 16 ደቂቃዎች ከመቀሌ አቻው ጋር ውድድር እንዲጨርስ ግዴታ ተጥሎበታል። 4ቱ ተጫዋቾቹ ለ3 ውድድሮች እንዳይጫወቱም እገዳ ተጥሎባቸዋል።

የጣና ሞገድ የሚል ያሜ ያለው የባህር ዳር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾቹ  በመቀሌ ደጋፊዎች መደብደባቸው ሳይንሳቸው ክለባቸው የ450ሺ ብር ቅጣትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወስኖበታል። የመቀሌው ከነማ እግር ኳስ ክለብም 1 መቶ ሺ ብር ለይስሙላ ቅጣት እንደተጣለበትም ለማወቅ ተችሏል። የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች በያዝነው ግንቦት መጀመሪያ ከመቀሌ ከነማ ክለብ አቻው ጋር ትግራይ ድረስ ሄደው ሲጫወቱ በብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ስድብ በደጋፊዎች መሰደባቸው አይዘነጋም።

በተለይ በጨዋታው ጊዜ የተጎዳው የባህር ዳር ተጫዋች ከሜዳ ሲወጣ በወጌሻዎች ተወርውሮ ሲጣል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተቋርጦ ነበር። ተጨዋቾቹ ከመቀሌ እንዳይወጡ ታግደው እንደነበርም አይዘነጋም።

ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ቴሌቪዥና በአማራ ቴሌቪዥኖች እንዳይዘገብ ከተወሰነ በኋላ በመቀሌ ከንቲባ አቶ ዳንዔል አሰፋ የተመራ የልዑካን ቡድን ባህር ዳር ድረስ መጥቶ ሚስጥራዊ ስብሰባ ከአማራ ክልል ባለስልጥናት ጋር ሲያደርግ እንደነበር ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያስረዳል።

በመጨረሻም፣ የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥፋተኛ ተብሎ የገንዘብ ቅጣትና የተቋረጠውን ውድድር በ8 ተጫዋቾች ብቻ እንዲጨርስ፣ 450 ሺ ብርም እንዲከፍል ግዴታ ተጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ (ኢሳት) የጨዋታውን በረብሻ መቋረጥ ተከትሎ የነበረውን ሂደት ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል። ምን እንኳን ጥፋቱ የመቀሌው ክለው ነው ቢባልም፣ የባህርዳር እግር ኳስ ክለብ የችግሩ መንስዔል ተደርጎ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል መግለጻችንም አይዘነጋም።