የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ መላኩ ፋንታ ከእስር ቤት ተጠርተው ተጠይቀዋል፤ የባንኩ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ መጥሪያ ደርሷቸዋል፤ የህወሃት መካላከያ አባላት ሰነድ አጥፍተዋል፤ ከአገር የወጡም አሉ።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን የሰሩትና የሙስና ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ መላኩ ፋንታ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ መሬት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ መረጃ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። አቶ መላኩ ለጥያቄ የተፈለጉት በሃላፊነት ላይ በነበሩባቸው አመታት ከህውሃት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ግለሰቦች “ ባላስቀመጡት ገንዘብ ልክ የብድር አገልግሎት ወስደው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል” ተብለው በተጠረጠሩት በጋምቤላ ክልል ከተፈጠረው የመሬት ዝርፊ ጋር በተያያዘ የክስ ዝግጅት እየተደረገባቸው ባሉ ባለሃብቶች ዙሪያ ባንኩ የተከተለውን አሳራር እና ቦርዱ ያሳለፈው ውሳኔ የሚያሳየው ሰነድ በመጥፋቱ ነው።
የውስጥ ምንጮቻችን እንደገለጹት በቤንሻንጉል ክልል “ሰባቱ ስታሮች” ተብለው የሚታወቁት እና ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስተሮች ከልማት ባንክ በወሰዱት እና ላለፉት ስምንት አመታት መሬት ተረክበው ጦም አሳድረዋል በተባሉት አቶ ሳለ እግዚአብሄር በርሄ፣ አቶ ኃይሉ ነጋ፣ ሻለቃ አዕምሮ ገ/ክርስቶስ፣ ሻለቃ ኪዱ ጣዕም፣ ኮማንደር ሙሉ ሁሉፍ፣ ኮማንደር ትርሃስ ገ/ዮሐንስ እና ጄኔራል ዮሐንስ አለም ሰገድ ከባንኩ ምንም አይነት ካፒታል ሳይቀበሉ በሽዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት በቢንሻንጉል ክልል የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት እንደሚሰሩ የፈቃድ ማስረጃ ከክልሉ በመቀበል 113 ሚልየን ብር ወስደው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ቦታ ሽያጭ እና የሪል እስቴት ንግድ ተሰማርተው ላለፉት ስምንት አመታት የወሰዱትን መሬት ጦም በማሳደር ለፈፀሙት ወንጀል በሌሉበት ክስ ለመመሰረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። መርማሪ ፖሊስ ግለሰቦቹን ከሚኖሩበት ዱባይ በኢንተርፖል ድጋፍ ለመያዝ የአቶ መላኩ ድጋፍ ያስፈልገኛል በማለት አቶ መላኩን ለማነጋገር ተገዷል።
አቶ መላኩ ምንም አይነት ማስረጃም ሆነ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ መላኩ “ ፍርድቤት ለሚያጣራው ጉዳይ ለፍርድ በሚቀርቡ አካላት እንጅ ከሀገር በወጡ እና በማይቀርቡ አካላት ዙሪያ ምንም ለመናገር ፈቃደኛ አይደለሁም” በማለታቸው መርማሪዎች የሚፈልጉትን ሳያገኙ ወደ እስር ቦታቸው ተመልሰዋል፡፡
በወቅቱ የቦርድ አመራር ለነበሩት አቶ አቢ ገ/መስቀል ፣ አቶ ያዕቆብ ያላ ፣ አቶ ሙሐመድ አህመድ፣ አቶ ተካ ይብራህ ፣ አቶ ነጋ ፀጋዬና አቶ አማረ ተክለማርያምም መጥሪያ እንደቀረበላቸው ታውቋል።
አገባብ ያለው የቴክኒክ ምርምራ ሳያደርጉ መንግስትን ለኪሳራ ዳርገዋል የተባሉትን በወቅቱ የአመራር አባላት የነበሩትን አንድ የባንኩ ኘሬዝዳንትና ሶስት ምክትል ኘሬዝዳንቶች እና የባንኩ ሥራ አስፈፃሚ የሥራ አመራር አባላትን ማለትም አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ የባንኩ ፕሬዝዳነት ፣ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ም/ ፕሬዝዳንት እና የብድር አገልግሎት፣ አቶ ገነነ ሩጋ፣ ም/ ፕሬዝዳንት እና የኮርፖሬት አገልግሎት፣ እንዲሁም አቶ ግርማ ወርቄ ም/ ፕሬዝዳንት ና የድጋፍ ሰጪ አገልግሎት ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል መረጃ በመሰብሰብ ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በልማት ባንክ ይተዳደሩ በነበሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ 349 ሚሊዮን 600 ሺ ብር ምዝበራ መፈጸሙን የደህንነት መስሪያ ቤት መረጃ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የማጣራት ስራ እንዲጀመር ለፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትእዛዝ ሰጥቷል። ጉዳዩ ከሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጋር እንደተያያዘና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል።
ለጠ/ሚኒስትር ቢሮ የቀረበው መረጃ “ በመንግስታት፤ በተቋማትና ወኪል ድርጅቶች ስም “ፈንዶችን” እንዲያስተዳድር በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ ልማት ባንክ ብሔራዊና ዓለምአቀፋዊ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አገር በቀል ድርጅቶች፣ የውጪ አገር መንግስታትም ሆኑ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት አንድም በተናጠል አልያም በጋራ ሆነው ለልማት የሚመድቧቸውን ፈንዶች ለማስተዳደርና ለታለሙት የልማት ፕሮግራሞች ወይም ፕሮጀክቶች በማዋል ዋነኛ የፋይናንስ መተላለፊያ የልማት ተቋም በመሆን እስከ 2002 ዓ.ም ባስተዳደራባቸው ዘጠኝ ዋነኛ የገንዘብ ምንጮች ላይ፣ 349 ሚልዮን 600 ሺ ብር ምዝበራ ተፈፅሟል” የሚል ነው። የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቀረበው መረጃ ላይ ተመስርቶ የማጣራት ስራ ጀምሯል።
“ምዝበራ ተፈጽሞባቸዋል ተብለው የተለዩት በልማት ባንክ የሚተዳደሩ የመንግስታት፤ የተቋማትና ወኪል ድርጅቶች ፈንዶች” የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ የሰጡባቸው ሲሆኑ እነዚህም፣ የቀድሞ ወታደሮችንና የጦር ጉዳተኞችን መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ፈንድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ፈንድ፣ የሐይቅ ዓሣዎች ልማት ፕሮግራም ፈንድ፣ የፓን አፍሪካ ምላሽ ሰጪ የተባይ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ፈንድ፣ የኢትዮ ኢጣሊያ የአርሲና ባሌ የብድር ፕሮግራም ፈንድ፣ ፋርም አፍሪካ ፈንድ፣ የስዊስ ስታቤክስ ፈንድ ፣ ከፊንላንድ መንግስት ለሰላሌ አርሶአደር የወተት ከብት ልማት ፓይለት ፕሮጀክት በብድር የተሰጠ ፈንድ እንዲሁም በገጠር የመብራት ኃይል ማስፋፊያ ፈንድ ናቸው።
አብዛኞቹ ምዝበራዎች የተፈጸሙት በነባር የህወሃት ታጋዮችና ወታደራዊ መሪዎች እንዲሁም በስልጣን ላይ ባሉ ታዋቂ ባለስልጣኖች ድጋፍ በመሆኑ፣ ምርመራው ውስብስብ ሊሆን እንደሚችልና ፖለቲካዊ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል። በተለያዩ የመካለከያ የስልጣን ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ከስልጣን የወረዱና ያሉ ባለስልጣናትን ለመክሰስ የሚደረገው ዘመቻ በቀጥታ በመከላከያ አዛዦች ላይ የተቃጣ ጥቃት ተደርጎ ሊታይና ያልታሰበ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል ምንጮች ግምታቸውን ያሰፍራሉ።
የኢትዩጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ ምዝበራ ከተፈጸመባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ባንኩ 107ኛ ዓመቱን ዘንድሮ አክብሯል፡፡ የመጀመሪያውና በኢትዮጵያ የልማት ባንክ ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነው የእርሻና የንግድ ማስፋፊያ የኢትዮጵያ ማኀበር ዳግማዊ አፄምኒልክ በፈቀዱትና ግንቦት 23 ቀን 19ዐ1 ዓ.ም ባስነገሩት አዋጅ መሠረት የዛሬ 107 ዓመት የተቋቋመ ነው፡፡
በአክስዮን መልክ የተቋቋመው ይኸው ማኀበር አቋሙ የታመነና ጠንካራ ይሆን ዘንድ በሚል ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መሥራች ማኀበርተኛ ሆነው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ከንጉሱና ንግስቲቱ በተጨማሪ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው፣ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ በጅሮንድ ሙሉጌታ ይገዙና ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደሚካኤልም ማህበርተኞች ነበሩ፡፡
ልማት ባንኩ በማሻሻያ ደንብ ቁጥር 116/1997 ዓ.ም እንደገና ሲቋቋም የተፈቀደ ካፒታሉ ወደ ብር 3 ቢሊዮን አድጓል፡፡ ልማት ባንኩ ሙሉ በሙሉ የመንግሥት ድርጅት ሲሆን የበላይ ተቆጣጣሪውም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲሆን ከተደረገ በሁዋላ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ በበላይነት ይቆጣጠረዋል ። በወቅቱ አቶ አሰፋ አብርሃ እና ኢንጂነር ግዛው ተ/ማርያም ባንኩን በበላይነት መርተውታል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ከሃላፊነት ከተነሱ በሁዋላ በአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ዘንድ ውዝግብ ተነስቷል።