ከሊዝ አዋጁ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የማዘጋጃ ቤት ገቢ በግማሸ አሸቆለቆለ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2004 ዓ.ም  10 ወራት ከማዘጋጃ ቤት ያገኘው ገቢ በግማሸ ማሸቆልቆሉን የኢሳት ምንጮች ገለጸዋል፡፡

አስተዳደሩ በተለይ በዋንኛነት ከሊዝና ከስም ዝውውር ጋር በተያያዘ ከሐምሌ 1 ቀን 2003 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ባሉት 10  ወራት 726 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ለማግኘት ያቀደ ቢሆንም ማሳካት የቻለው 363 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ብቻ ነው፡፡ይህም አፈጻጸም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 50 በመቶ ያህል ሆኗል፡፡ለአፈጻጸሙ መቀነስ ዋንኛ ምክንያት በዚህ ዓመት የወጣው አወዛጋቢ የሊዝ ማሻሻያ አዋጅ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ነው፡፡

የማዘጋጃ ቤት ገቢ ማሸቆልቆል በ10 ወሩ የሚገኘውን አጠቃላይ ገቢ ዕቅድ እንዳይሳካ እንቅፋት መሆኑም ተገልጿል፡፡ከቀጥታ ታክስ፣ቀጥታ ካልሆነ ታክሰ፣ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ በ10 ወሩ በድምሩ 4 ነጥብ 88 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 4 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር ወይም የእቅዱን 91 በመቶ ያህል ነው፡፡

አንድ በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ባለሃብት እንደገለጹት የሊዝ አዋጁ ማሻሻያ ከወጣና ውዝግብ ካሰከተለ በኃላ ገበያቸው በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዙን አረጋግጠዋል፡፡“ አንድ ሰው የገዛውን ቤት እንደፈለገ መሸጥ፣ መለወጥ ካልቻለ ለምን ይገዛል”ሲሉ የሚጠይቁት እኙሁ ባለሃብት “አዋጁ ቤት የምትሸጠው ቆርቆሮና ግድግዳውን እንጂ መሬቱን ጭምር አይደለም፡፡የሊዝ መብት ማስተላለፍ የሚችለው መንግስት ነው ተብሏል፡፡ይህ ዓይነቱ ሕግ በተለይ ለሪልስቴት ባለሃብቱ ቀጣይ እንቅስቃሴ ፈታኝ ነው” ብለዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም በድንገት ፓርላማ ቀርቦ ቋሚ ከሚቴ እንኳን ሳይመክርበት በአፋጣኝ የጸደቀውና ከህዳር 28 ቀን 2004 ጀምሮ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ ሥራ ላይ የዋለው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አሁን ድረስ በማወዛገብ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ከራሱ ሰዎች ጭምር በቀጥታና በተዘዋዋሪ የገጠመው ተቃውሞ ከመፍታት ይልቅ “ችግሩን የሚፈጥሩት ጥቅማቸው የተነካ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው” ወደሚል ክስ ውስጥ መግባቱ ይበልጥ ነገሩን አወሳስቦት ይገኛል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide