ከህዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ ቅናሽ መደረጉን ተከትሎ በአዲስአበባ  የነዳጅ ማደያዎች ባለፈው አንድ ሳምንት የታየው የነዳጅ ሰልፍ አሁንም ድረስ መቀጠሉ ታወቀ፡፡

ታኀሳስ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ንግድ ሚኒስቴር የዋጋ ቅናሹን ካደረገ በሃላ ማደያዎች አዲሱ ታሪፍ አያወዋጣንም በሚል መናገራቸውን ተከትሎ የአቅርቦት እጥረት የተፈጠረ ሲሆን ሚኒስቴሩ የተወሰኑ ማደያዎችን በማሸግና በማስፈራራት ነገሩን ለማርገብ ቢሞክርም ችግሩ ሳይቀረፍ  8ኛ ቀኑን ይዞአል፡፡

በቦሌ፣ በካዛንቺስ፣ በንፋስስልክ በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች በየማደያው ረጃጅም ሰልፎች የሚታዩ ሲሆን የችግሩ ትክክለኛ መንስኤ ምን እንደሆነ እንዳላወቁያ ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች ገልጸው፣  ነዳጅ ለመቅዳት ከማደያ ማደያ መዞር እና ባለበት ቦታም ወረፋ ጠብቆ ለመቅዳት ቢያንስ ለሁለት ሰዓታት ያህል በመቆም የሥራ ሰዓታቸውን እያቃጠሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ችግሩን መቅረፍ አለመቻሉም እንዳሳዘናቸው ጨምረው ተናግረዋል፡፡