ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የጸጥታና የደህንነት ሃላፊዎች በናዝሬት ከተማ ተሰበሰቡ

ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞች ዳግም የተቀሰቀሰውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ተከትሎ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የጸጥታና የደህንነት ሃላፊዎች በናዝሬት አዳማ ከተማ ሃገር አቀፍ ምክክር ጀመሩ።

በዚሁ በሶስት ቀናቶች በሚቆየው ሃገር አቀፍ የጸጥታ ምክክር ከ200 በላይ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዲሁም ከፍተኛ የጸጥታ ስራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

በአይነቱ የመጀመሪያው ነው በተባለው በዚሁ የጸጥታና የደህንነት ሃላፊዎች ምክክር በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ያለው ተቃውሞ በምን መልኩ ለመፍታት እንደሚቻል በሰፊው ውይይት እያካሄደ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት በክልሉ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ውሏል ካሉ በሁዋላ እንዲህ ያለ አገር አቀፍ የጸጥታ ምክክር ሲያካሄዱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች በመጓዝ ተቋርጦ የሚገኘውን የዩንቨርስቲ ትምህርት ለማስቀጠል ድርድር ኣያደረጉ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄን በማቅረብ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለው እርምጃ በአስቸኳይ መቆም እንደሚገባው በማሳሰብ ላይ ናቸው።

በዩንቨርስቲዎች ውስጥ የሚወረወሩ የእጅ ቦንቦችም ለደህንነታቸው ስጋት ፈጥረው እንደሚገኙ በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ በዲላና ጅማ ዩኒቨስቲዎች በደረሱ የቦምብ አደጋዎች በትንሹ ሁለት ተማሪዎች መገደላቸው ይታወሳል። ድርጊቱን ያረጋገጠው መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር እየተካሄደ ነው ቢልም እስካሁን ድረስ ስለጥቃቱ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።