መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ባወጣው መገለጫ “ገዢው ፓርቲ የህዝብን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ደግፈን በመቆማችን የኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን መክሰስ ገፍቶበታል” ብሎአል።
“ገዥዉ ፓርቲም የችግሩ መንስኤ የኦሮሚያ ክልል አካሉ ኦህዴድ መሆኑን በሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች ቢገልጽም፣ ለጥፋቱ ይቅርታ እንደመጠየቅ ፋንታ ባለፉት አራት ወራት ዉስጥ ዉስጥ ብቻ ከ270 በላይ የኦሮሞ ዜጎች ገድሏል፤ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ ንፁሐን ዜጎች አስሯል፣ ከቀያቸውም እንዲፈናቀሉ አድርጓል” ብሎአል።
“የኢህአዴግ መንግስት ባለሥልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን እየከሰሱ ነው” ያለው ኦፌኮ፣ መንግስት ከሁለት መቶ ሰባ በላይ ለተገደሉ ዜጎች ሙሉ ኃላፊነት መዉሰድ አለበት ብሎአል።