(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2010) የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ከመንግስት ጋር የተናጠል ድርድር ጀመረ።
ቀጣዩን ድርድር በአዲስ አበባ ለማካሄድ የኦዴግ መሪዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ እንደሚገቡም ተገልጿል።
በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ድርድሩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ከመንግስት ከተላኩ ሁለት ልኡካን ጋር መወያየቱን ገልጿል።
የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ እንዳመለከተው ከመንግስት ልኡካን ጋር ድርድሩ የተካሄደው ባለፈው አርብና ቅዳሜ ነበር።
ውይይቱ የተካሄደበት ስፍራ ግን በግልጽ አልተቀመጠም።
በመንግስት ወገን እነማን እንደተወከሉ በኦዴግ በኩልም እነማን እንደቀረቡም የተባለ ነገር የለም።
ከኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ልኡካን ጋር መነጋገሩን በመግለጫው ያመለከተው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/በሃገሪቱ የሚታዩት የማሻሻያ ርምጃዎች እንዲሰፉ፣እንዲጎለብቱና ጥልቀት እንዲኖራቸው ባለው ፍላጎት ድርድሩ ውስጥ መግባቱን አመልክቷል።
እየታየ ባለው የማሻሻያ ርምጃ መበረታታቱንም አስታውቋል።
የተጀመረውን ውይይት ለመቀጠል የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራሮች በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት እንደሚሄዱም ተገልጿል።
ይህም ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚሆንም ተመልክቷል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/ለለውጥ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያካሂዱም ጥሪ አቅርቧል።
ኦዴግ ከአርበኞች ግንቦት ሰባትና ከሌሎች 2 ድርጅቶች ጋር በፈጠረው ሃገራዊ ንቅናቄ የተናጠል ድርድር እንደማይኖር ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህ የተናጠል ድርድር ከንቅናቄው እውቅና ውጪ መሆኑም ተመልክቷል።