ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2009)
የኦሮሞ ህዝብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ኪሳራ የተለየ ጥቅም ባልፈለገበት ሁኔታ በሃገሪቱ ያለው አገዛዝ አዲስ አበባ በተመከተ ያወጣቅ ረቂቅ ህግ ተቀባይነት እንደሌለው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ገለጸ።
ድርጅቱ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ይኖረዋል የተባለው ልዩ ጥቅም አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አዲስ አበባ ከተማ በሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ኪሳራ የኦሮሞ ህዝብ ለመጠቀም እንደፈለገ ተደርጎ የተቃኘውና በውዥንብር የተሞላው ረቂቅ ህግ ለህዝቡ የሚያስገኘ ጥቅም የለም ብሏል ።
የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ይኖረዋል የተባለን ልዩ ጥቅም የተመለከተው ረቂቅ ህግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለሚቀጥለው አመት መተላለፉ ተነግሯል።
ረቂቅ ህግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለፓርላማው ቢመራም እንደገና በህዝብ ተወካዮች ለህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ኮሚቴ ለተጨማሪ እይታ በሚል ተላልፏል።
በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ጉዳዩ ከታየ በኋላ በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል በተባለው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላት ልዩ ጥቅም የሚተነትነው ከወዲሁ የተለያዩ የተቃውሞ አስተያየቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግምባር (ኦዴግ) የህግ ረቂቁን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ልዩ ጥቅሙ የኦሮሞን ህዝብ የማይጠቅም ነው ሲል ኮንኖታል። ምክንያት ያደረገው ደግሞ በረቂቅ ህጉ ከተካተቱት ጉዳዮች ብዙዎቹ ማንም ቢሆን ሰው በመሆኑ ሊያገኛቸው የሚገቡ መብቶች በመሆናቸው ነው ብሏል። የኦዴግ ስራ አስፈጻሚና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ሌንጮ ባቲም ይህንኑ አረጋግጠዋል። እንደ ኦዴግ መግለጫ የኦሮሞ ህዝብ የጠየቀው መሰረታዊ መብቶቹ እንዲከበሩ እንጂ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ኪሳራ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ አይደለም። እናም ረቂቅ ህጉ የኦሮሞን ህጋዊ እና ወሳኝ ጥያቄዎች ያሟላ አይደለም ሲል ኦዴግ አዲስ አበባን በተመለከተ ልዩ ጥቅም የተባለውን ሰነድ አውግዞታል። ኦዴግ በመግለጫው የኦሮሞ ህዝብ አዲስ አበባን በተመለከተ የወሰነውን ማስተር ፕላን ቢቃወመውም በረቂቅ ህግ ስም ተመልሶ መምጣቱ የሚያስገርም ነው ብሏል።