ኦነግ የዶ/ር አብይን መመረጥ ወያኔ በኦሮሞ ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ለማስፋፋት የወጠነው ማባበያ ነው አለ
ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል
(ኢሳት ዜና መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) ኦነግ በመግለጫው በ27 ዓመታት ኢህአዴግ ስርዓት አገዛዝ ዘመን ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ችግር አለመፈታቱንና ወደ ባሰ ሁኔታ መሸጋገሩን ገልጾ፣ የወያኔ ስርዓት አስተማማኝ መፍትሄ ለማግኘት ከመስራት ይልቅ በማባበያና እውን በማይሆን ተስፋ ዓላመውን ማሳከቱን መርጧል ብሎአል። ይህ ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ይሁን በኦነግ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል።
ኦነግ ያለውን የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ፣ በኦነግና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የሚደረግ ንግግር ሶስተኛ ወገን ባለበትና ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲከናወን ጥሪ አቅርቧል።
ኦነግ በመግለጫው ከኢህአዴግ ጋር የተደረጉና የከሸፉ ድርድሮችን ዘርዝሮ ያቀረበ ሲሆን፣ ለእነዚህ ድርድሮች መክሸፍ ኢህአዴግን ተጠያቂ አድርጓል።
ኦነግ ያለውን ችግር ያላንዳች ፍራቻ ግልጽ አውጥቶ መወያየትና የታወጀውን ጦርነት ገትቶ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መቋጫ ማበጀት ከኢትዮጵያ መንግስት ይጠበቃል ብሎአል።