ኦብነግ የተኩስ አቁም አደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 7/2010)የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታወቀ።

የግንባሩ አመራሮችም በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል።

እስከዛሬ ድረስ በግንባሩ ስም ተደርጉ ከተባሉ ስምምነቶች በተለየ ይህንን ውሳኔ ግንባሩ በራሱ ድረ ገጽም ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/ከእሁድ ነሐሴ 6/2010 ጀምሮ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጉን ነው ያስታወቀው።

እሁድ ቀትር ላይ ይፋ በሆነው የተናጠል የተኩስ አቁም በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ተቋማት ላይ ሲወሰዱ የነበሩ ርምጃዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚቆሙ ኦብነግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ተመሳሳይ ርምጃ በመውሰድ ምላሽ እንዲሰጥ ኦብነግ ጥሪ አቅርቧል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎም የግንባሩ ልኡካን አዲስ አበባ ገብተዋል።

በኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድ ሄርሞጊ የተመራውና ሶስት አባላትን ያቀፈው ቡድን ትላንት አዲስ አበባ ሲገባ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውለታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቀውስ ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተረጋጋ መምጣቱን መረጃዎች አመልክተዋል።

ግጭቱን የቀሰቀሱትና የመሩት የክልሉ ባለስልጣናት መሆናቸውም ተጋልጧል።

የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ግጭቱን በማባባስ ሲሰራ መቆየቱም ይፋ ሆኗል።

ትላንት ጅጅጋ ላይ በተካሄደ ሕዝባዊ ጉባኤ ላይ የተገኙት የመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሰራዊቱ ወደ ክልሉ የገባው የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ በላይ በአመጽ ድርጊቱ እንዲቀጥል እንደማይፈቀድለትም የመከላከያ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ሐምሌ 28/2010 ጅጅጋ ላይ ከተጀመረው የተደራጀ ዘረፋና ግድያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ሙሉ በሙሉ የንግድ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ክልሉ ሲያደርግ የነበረውን በረራ አቋርጧል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከስልጣናቸው መነሳታቸው ይታወቃል።

አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሶሕዴፓ ሊቀመንበርነታቸው የቀጠሉ ቢሆንም በሳምንቱ መጨረሻም ከዚህ ሃላፊነታቸው መነሳታቸው ተመልክቷል።

በምትካቸውም አቶ አህመድ ሽዴ የሊቀመንበርነቱን ቦታ እንዲረከቡ ተደርጓል።

አቶ አህመድ ሽዴ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ መሆናቸው ይታወቃል።

የሶማሌ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ሶሕዴፓ/የሚመራው የክልሉ መንግስት ምክር ቤት ለክልሉ አዲስ ፕሬዝዳንት ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ ባለስልጣናት ያለመከሰስ መብትም ይነሳል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ነው።