(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2010)
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር ባደረገው ውጊያ በርካታ ወታደሮችን መግደሉንና ማቁሰሉን አስታወቀ።
የኦጋዴን የዜና ወኪል የኦብነግን አባል ጠቅሶ እንደዘገበው ውጊያው የተካሄድው ታህሳስ 30/2010 ነው።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገው ውጊያ በመንግስት በኩል ማርጋገጫ ባይገኝም የመንግስት ወታደሮች መገደላቸውና መቁሰላቸው ተመልክቷል።
በጃሌሎ መንደር ተደረገ በተባለው በዚህ ውጊያ ከወታደሮቹ መገደልና መቁሰል በተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች፣ጥይቶችና የመገናኛ መሳሪያዎች መማረካቸው ተገልጿል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ተደረገ ስለተባለው ውጊያ ከገለልተኛ ወገን የተባለ ነገር የለም ።
ኦብነግ በተደጋጋሚ በኦጋዴን አካባቢ በህወህት ሰራዊት ላይ ጥቃት እየሰነዘረ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ድርጀቱ ከዚህ ቀደም በነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ በነበረው የቻይና ኩባንያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር 74 የኩባንያው ሰራተኞችን መግደሉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የህወሃት አገዛዝ በሶማሌ ክልል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት በሚል አካባቢውን ለአለማቀፍ መገናኛ ብዙሀንና የእርዳታ ድርጅቶች ዝግ በማድረግ የጅምላ ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።