ኦብነግ ከህዋሃት ጋር ድርድር የይስሙላ ነው አለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 29/2010) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/ በቅርቡ ከኢትዮጵያው አገዛዝ ባለስልጣናት ጋር ያካሄደው ድርድር የይስሙላና የማይጨበጥ መሆኑን የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባል ገለጹ።

የኦብነግ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኢንፎርሜሽን ዘርፍ ሃላፊው አቶ ሃሰን አብዱላሂ እንደገለጹት የኢትዮጵያው አገዛዝ በድርድር ስም የሚያካሄደው እንቅስቃሴ የውሸትና ለማስመሰል የሚደረግ ነው።

እናም ኦብነግ ካለቀለት ስርአት ጋር ድርድር መቀጠል እንደማይፈልግ ሃላፊው ገልጸዋል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ ስራ አስፈጻሚና የኢንፎርሜሽን ሃላፊው አቶ ሐሰን አብዱላሂ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እንዳሉት ድርጅታቸው በሕወሃት/ኢህአዴግ ከሚመራው አገዛዝ ጋር ድርድር ለማድረግ የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 ነበር።

በዚያን ወቅት የኬንያ ፕሬዝዳንት በነበሩት መዋይ ኪባኪ አደራዳሪነት ሂደቱ ቢጀመርም አገዛዙ ሕገ መንግስቱን ተቀበሉ የሚል ቅድመ ሁነታ በማቅረቡ ኦብነግ ከውይይቱ ከ 6 አመታት በፊት አቋርጦ መወጣቱን ነው የተናገሩት።

አሁን ደግሞ በስልጣን ላይ  የሚገኙት የኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ድርድሩን ቀጥሉ ሲሉ በመጠየቃቸው አለምአቅፉን ማህበረሰብና ፕሬዝዳንቱን በማክበር ከአገዛዙ ጋር በናይሮቢ ውይይት ለማድረግ ቢሞከረም ሂደቱ የይስሙላና የተጨበጠ አለመሆኑን አቶ ሐሰን አብዱላሂ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሕወሐት አገዛዝ እርስ በርሱ የተከፋፈለ በመሆኑ ከማንም ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይቻልም አቶ ሀሰን አብዱላሂ ይገልጻሉ።

እናም ወይይቱ መቋረጡንና ስምምነት የሌለበት በመሆኑ ድርድር የሚባል ነገር የለም ነው ያሉት። ሕወሀት ሴረኛ አገዛዝ እንደሁነ የገለጹት አቶ ሐሰን አብዱላሂ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልልሎች መካካከል ግጭት እንዲፈጠር ማድረጉን አስታውቀዋል።

በሁለቱ ወንድማማች ሕዝብ መካከል የሕወሐት ጄኔራሎች ሆን ብለው ግጭት በመፍጠር እስከ 1 ሚሊየን ሰዎች አፈናቅለዋል ሲሉም  የኦብነጉ ስራአስፈጻሚ አቶ ሐሰን አብዱላሂ ገልጸዋል።

እናም አገዛዙ ከስልጣን እስኪወገድ ድረስ ከሊሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ትግላቸውን እንደሚቀጥሉም አስታወቀዋል።