ኢሳት (ሰኔ 20 ፥2009)
ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን መብት የተመለከተው ረቂቅ ኣዋጅ በሚንስትሮች ም/ቤት መጽደቁ ተሰማ። በቀጣዩ ሳምንት ፓርላማ ቀርቦ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል።
ከሳምንት በፊት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተወያይቶ ያሳለፈው ይህ ረቂቅ ኣዋጅ አዲስ አበባ የሚባለው የከተማው ስያሜ በነበረበት እንዲቀጥል ፊንፊኔ የሚለውም መጠሪያ በተጨማሪነት እንዲያገለግል ወስኗል።
በሚኒስትሮች ም/ቤት ማክሰኞ እለት የጸደቀው ረቂቅ አዋጅ ኦሮምኛ ከአማርኛ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የፈቀደ ሲሆን የአከባቢ መጠሪያ ስሞች እንደአስፈላጊነቱ ወደ ቀድሞ ስማቸው እንደሚመለሱም አስፍሯል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰራተኞች የሆኑና ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ እንደ አዲስ አበባ መስተዳድር የመንግስት ሰራተኞች ጋር መኖሪያ ቤቶችን የሚያገኙበትን መብት ይሰጣል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለመንግስታዊና ማህበራዊ ተቋማትና ሌሎች ቦታዎችን ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙ የሚፈቅደው ይህ አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ውሃን የማድረስ አና የመሳሰሉ መብቶችን የሚሰጥ ሲሆን በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ውሃን የማመንጨትና ደረቅ ቆሻሻን የማስወገድ ስራዎችም በጋራ እንደሚሰራም ተመልክቷል። የትራንስፖርት አገልግሎት አውቶቡስና ባቡርን ጨምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች የአዲስ አበባ መስተዳደር እንዲያቀርብም በህጉ ላይ ተመልክቷል።
በአዋጅ የተቀመጡትን መብትና ጥቅሞች በተመለከተ ለማስፈጸም ከአዲስ አበባ መስተዳድርና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ ም/ቤት እንደሚመሰረት የተገለጸ ሲሆን ይህ የጋራ ም/ቤት ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት እንደሚሆንም ማክሰኞ ሰኔ 20/2009 በሚኒስትሮች ም/ቤት የጸደቀው አዋጅ ይደነግጋል። ይህ አዋጅ በስራ ላይ የሚውለው በቀጣዩ ሳምንት በፓርላማ ቀርቦ ከጸደቀና በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ከታተመ በኋላ እንደሚሆንም መረዳት ተችሏል።
ቀደም ሲል በረቂቁ ላይ በዝርዝር ቀርበው የነበሩ ጉዳዮች በአዲሱ ወይንም በሚኒስትሮች ም/ቤት በጸደቀው ላይ መታለፋቸውንም መረዳት ተችሏል።