ኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2009)

ኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጸ።

ግጭቱ ተቀስቅሶባቸዋል በተባሉት አካባቢዎች ከመሬት ይዞታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ሲካሄዱ መቆየታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሁላቱ አጎራባች አካባቢዎች ግጭት መኖሩን ቢገልጽም የሟች ቁጥርን ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑ የተወሰኑ ወረዳዎች የተከሰቱት ግጭቶች እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ይሁንና ሃላፊው በሰውና በንብረት ላይ ደርሷል ስላሉት ሁኔታ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ የሁለቱ ክልሎች ሃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ስለተከሰተው የድርቅ አደጋ ሪፖርት ያወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሌ ፣ በአፋር፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ከድርቅና ግጭቶች ጋር በተገናኘ ከ23 ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ድርጅቱ በአካባቢ አለ ስላለው ግጭት ግን መረጃን ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ የተፈናቀሉት ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን የሚፈልጉ እንደሆነ አመልክቷል። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ትኩረት ለማስለወጥ የብሄር ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።