ኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ለማን መገርሳን ደግሞ ምክትል ሊ/መንበር አድርጎ መረጠ
(ኢሳት ዜና የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) ድርጅቱ እንዳስታወቀው ኦህዴድን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን በደ/ር አብይ አህመድ ለመተካት በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔው ኦህዴድ ዶ/ር አብይን ጠ/ሚኒስትር አድርጎ በእጩነት ለማቅረብ ፍላጎት ያለው መሆኑን አስተያየቶች ያመለከታሉ፡
ሰሞኑን የኦሮሞ የፖለቲካ አክቲቪስቶች አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮምያ ክልል ወጥተው የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ እንዲይዙ አስተያየቶችን ሲሰጡ ሰንብተዋል። ይሁን እንጅ ኦህዴድ ከአቶ ለማ ይልቅ ዶ/ር አብይን ለጠ/ሚኒስትርነት ቦታ እጩ አድርጎ ለማቅረብ እንዲችል፣ የድርጅቱን ሊ/መንበርነት ቦታ ለእርሳቸው መስጠቱን መርጧል። በኢህአዴግ የድርጅት አሰራር ጠ/ሚኒስትር የሚሆነው ሰው ኢህአዴግን ከመሰረቱ ድርጅቶች ውስጥ የአንዱ ድርጅት ሊቀመንበር መሆን አለበት።
ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ለማ መገርሳ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ለምን አልፈለጉትም የሚለው ጥያቄ የማህበራዊ ሚዲያው የመወያያ አጀንዳ ሆኗል። ኦህዴድ በደንብ መክሮበት ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሆነ የሚገልጹ ያሉትን ያክል፣ ውሳኔውን ለመቀበል የተቸገሩ ወገኖችም መኖራቸውንም እየገለጹ ነው።
የህወሃት የስራ አስፈጸማ አባል የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ለማ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆን፣ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመውሰድ እንደሚችሉ ለብሉምበርግ ጋዜጣ ተናግረው ነበር።