ኦህዴድ ከ18 ሺ በላይ አባላቱ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

የካቲት ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ ባወጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በኦሮምያ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ 4 ሺ 460 ነባር አመራሮችና 13 ሺ 578 የቀበሌ አመራሮች ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡ እርምጃ በተወሰደባቸው ሰዎች ቦታ ላይ 5 ሺ 832 አዳዲስ አመራሮችን መተካቱን ገልጿል።
በክልል እና በወረዳ ደረጃ በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት እርምጃ ከተወሰደባቸው 964 ሰዎች መካከል 260 ለህግ ይቀርባሉ ብሎአል። በቀበሌ ደረጃም 2 ሺ 470 አመራሮችን ለህግ ለማቅረብ መረጃ የማሰባሰብና ክስ የመመስረት ስራ እየተሰራ ነው ሲል ገልጿል። እስካሁን ከታገዱት ባለስልጣናት ጋር በተያያዘ 7 ሚሊዮን 149 ሺ 32 ብር በጥሬ ገንዘብ፣ 4 ተሽከርከሪዎች፣ 40 መኖሪያ ቤቶች ፣ ሁለት ህንጻዎች፣ 244 ሺ 356 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት እንዲሁም 54.8 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት መታገዱን ገልጿል።
በተቀሩት አመራሮች ላይ የማጣራቱ ስራ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ድርጅቱ፣ የታገደው ገንዘብም ከተመዘበረው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ 15 ሺ በሚሆኑት የኦህዴድ አባላት ላይ የወሰደውን እርምጃ በዝርዝር አላስታወቀም። አባላቱን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በማዘዋወር መልሶ ሊሾማቸው እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።