ኦህዴድ አቶ ሙክታር ከድርንና ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከሃላፊነት አሰናበተ

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል ለወራት ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሙክታር ከድርንና ምክትል ሊቀመንበሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከሃላፊነት አሰናበተ።

በተሰናበቱት የኦህዴድ አመራሮች ምትክ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉ ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰሞኑን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን እንዲካሄድና በአመራሮቹና በአባላቱ ላይ ግምገማ ማካሄዱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከወራት በፊት አካሄዶት በነበረው ግምገማ ለህዝባዊ ተቃውሞ መፍትሄን አላመጡም ባላቸው አባላትና የክልሉ ሃላፊዎች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ከፓርቲው ሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት አመራሮች በኦህዴድ ማዕከላዊ አባላት ዘንድ መጠነ ሰፊ ግምገማ እንደተካሄደባቸውና አመራሮቹም የቀረቡባቸውን ትችቶች መከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

አቶ ሙክታር ከድር ከፓርቲው ሃላፊነታቸው ቢሰናበቱም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው በሃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ ታውቋል።

ይሁንና የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት በቀጣዩ ወር በሚካሄደው ልዩ ጉባዔ ወቅት አቶ ሙክታርን ከፕሬዚዳንትነት በማንሳት አቶ ለማ መገርሳን የኦህዴድ ሊቀመንበት አድርጎ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

የመንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ላለው ህዝባዊ ተቃውሞ የክልል አመራሮችን ተጠያቄ በማድረግ ሃላፊነታቸውን አልተወጡም ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ለወራት በቆየው የክልሉ ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ ዳኞች እና ሲቪል ሰራተኞች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እንዲነሳ አድርጋችኋል ተብለው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ ፓርቲው አሁንም ድረስ ግምገማን እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።

የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ለበርካታ አመታት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ማገልገላቸው የሚታወስ ነው።

ከክልሉ ለወራት ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሂውማን ራይትስ ዎችና የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልፅ ቆይተዋል።