ኦህዴድ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ኦሕዴድን ከሚወክሉ 45 አባላት አስሩን አባረረ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2010)

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ውስጥ ኦህዴድን ከሚወክሉ 45 አባላት አስሩን ማባረሩ ታወቀ።

ሙክታር ከድር እና ወይዘሮ አስቴር ማሞ

ማዕከላዊ ኮሚቴው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በመንግስት የተነፈጋቸውን ጥቅማ ጥቅም ኦህዴድ እንደሚያሟላም ቃል ገብቷል።

በውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከተቃዋሚዎች ጋር ጭምር ተባብሮ ለመስራትም ውሳኔ ማሳለፉ ተመልክቷል።

በአዳማ በመካሄድ ላይ ያለው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ቀጥሏል።

በግል ተወዳድረው የፓርላማ አባል በመሆናቸው ሲያገኙት የነበረው ጥቅማ ጥቅም ሙሉ በሙሉ የተቋረጠባቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የሚጓጓዙበት ተሽከርካሪ ጭምር ስላልነበራቸው በከተማ ታክሲና አውቶቡስ ሲጠቀሙ መቆየታቸው ተመልክቷል።

በፓርላማ በአዋጅ የጸደቀላቸውን የጡረታ መብታቸውን ጭምር ተነፍገው ባለፉት 12 አመታት ያለ ቋሚ ገቢ ሕይወታቸውን ሲመሩ ለቆዩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ተሽከርካሪና ሕክምናን ጨምሮ ጥቅማ ጥቅም እንዲጠበቅላቸው በአዳማ በማካሄድ ላይ ያለው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መወሰኑ ታውቋል።

ለ10 ቀናት ይቀጥላል የተባለውና በአዳማ እየመከረ ያለው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ድርጅቱን ወክለው በኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሚሳተፉ 45 ሰዎች 10ሩን በማባረር በሌሎች መተካቱም ይፋ ሆኗል።

ከተባረሩት ውስጥ የቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ሙክታር ከድርና ወይዘሮ አስቴር ማሞ እንደሚገኙበትም ታውቋል።

በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በውጭ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ጭምር አብሮ እንደሚሰራም ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው ገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን /ኦ ቢ ኤንም/ ነጻነቱን ጠብቆ ስርጭቱን እንዲቀጥል መወሰኑም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የንግድ ሁኔታ የተዛባ እንደሆነ የገመገመው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በዚህ ረገድ የማስተካከያ ስራ መሰራት እንዳለበትም ማሳሰቡ ታውቋል።

በዚህ ረገድ የኦሮሞ ሕዝብ ተገቢውን ጥቅም አላገኘም ሲል መገምገሙንም ይፋ የሆኑት ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ስልጣንን ተገን ያደረገ የተዛባ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩንም ገምግሟል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሞ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኦህዴድ እንደሚሰራም በማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ተወስኗል።