ጥቅምት ፩(አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አስተዳደሩ ቀደም ሲል በወር 530 ሺ ብር ገደማ ቤት በመከራየት ውል ከፈጸመ በኋላ ከሕዝብ በተከታታይ ተቃውሞ መሰማቱን ተከትሎ እንዲሰረዝ በመወሰን ለሁለተኛ ጊዜ 400 ሺ ብር የሚያወጣ ቤት በአዲስአበባ አክሱም ሆቴል አካባቢ መከራየቱ ሌላ ተቃውሞና ውግዘትን እያስከተለበት ይገኛል፡፡ አስተዳደሩ ፕሬዚደንቱ በመስከረም ወር 2006 ስልጣን እንደሚያስረክቡ አስቀድሞ እያወቀ ምንም ዓይነት ዝግጅት ሳያደርግ በመጨረሻው ሰዓት ወደቤት መከራየት ሩጫ የገባበት ሁኔታ ማነጋገሩን ቀጥሎአል፡፡
የዜናው ምንጭ ለተሰናባቹ ፕሬዚደንት የሚወጣው ኪራይ ከፍተኛ አመራሩን ጭምር ለሁለት የከፈለና ያወዛገበ እንደነበር ጠቁሞ በአሁኑ ወቅት በአስቸኩዋይ ተለዋጭ ቤት ተፈልጎ ውሉ እንዲሰረዝ ተወስኖ ወደአፈጻጸም ተገብቶአል ብሎአል፡፡ በመሆኑም አቶ ግርማ ተለዋጭ ቤት አስኪገን ብቻ በዚህ ቤት ውስጥ ከሶስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ሊኖሩበት እንደሚችሉ ምንጫችን ገምቷል፡፡
አቶ ግርማ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም 12 ዓመታት የቆዩበትን ስልጣን ለተተኪያቸው ካስረከቡ በኋላ ዕለቱኑ ቤተመንግስቱን ለአዲሱ ፕሬዚደንት በማስረከብ ወደተዘጋጀላቸው ቤት ተዛውረዋል፡፡
ለአቶ ግርማ መኖሪያ ቤት በወር ሊወጣ የታሰበው 400ሺ ብር ጉዳይ ከተሰማ በኋላ በተለይ ሳይተርፈው ለአባይ ግድብ እየተባለ የወር ደመወዙን የሚገብረውን መካከለኛ ገቢ ያላውን ሰራተኛ ነገሩ ማሳዘኑ የሚታወስ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የቤተመንግስት አስተዳደር በቤተመንግስት ውስጥ ያሉ ቅርሶችን ሙዚየም በመገንባት ሊያደራጅ ነው፡፡
አስተዳደሩ ለዚሁ ስራ ዘንድሮ ዳጎስ ያለ በድምሩ 225 ሚሊየን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 147 ሚሊየን ብር ያህሉ በቤተመንግስት ውስጥ ያሉትን ቅርሶች፣ለማደራጀትና አዲስ ሙዚየም ለመገንባት፣ጥንታዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመሳሰሉት ተግባራት እንደሚያውለው ምንጫችን ጨምሮ ጠቅሶአል፡፡