(ኢሳት ዜና–መስከረም 19/2010) በአፋር ክልል በአምቤዬራ ዞን፣በጅማ፣በደቡብ ምስራቅና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ93 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተሰማ።
የአፍሪካ ጋዜጠኞች ማዕከል/ሲ ኤ ጄ/ እንደዘገበው አዲስ አበባን በሚያዋስኑ ልዩ ዞኖችና በተጠቀሱት አካባቢዎች ካለማቋረጥ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ 18 ሺ 628 ቤተሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የአፍሪካ ጋዜጠኞች ማዕከል/ሲ ኤ ጄ/ ዘገባ እንዳመለከተው ከ93 ሺ በላይ ሰዎችን ከቀያቸው ያፈናቀለው የጎርፍ አደጋ የተከሰተው በአፋር ክልል በአምቤዬራ ዞን፣በጅማ፣በደቡብ ምስራቅና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው።
ካለማቋረጥ የጣለው ዝናብ በአካባቢዎቹ ባስከተለው ጎርፍም 18 ሺ 628 ቤተሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሶማሌና በኦሮሞ አዋሳኝ ወረዳዎች ሰሞኑን የተከሰተው ግጭትና የተከተለው መፈናቀል ብሎም በጎርፉ የደረሰው አደጋ ተጨምሮ በአካባቢው ያለውን ችግር እንዳባባሰው ዘገባው አመልክቷል።
የጎርፍ አደጋው፣ግጭቱና መፈናቀሉ የተከሰቱት በተለያዩ አካባቢዎች ቢሆንም በተመሳሳይ ጊዜ መከሰቱ ግን አደጋውን ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ከባድ እንዳደረገው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ማዕከል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለስልጣናትን በመጥቀስ ዘግቧል።
የደረሰውን አደጋ የሚያጣራና በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በተዘጋጁ ጊዜያዊ መጠለያዎች የሚያስፈልገውን እርዳታ የሚያጠና ቡድን የቀይ መስቀል ማህበር ማሰማራቱንም ለማወቅ ተችሏል።
በጎርፉ ለተፈናቀሉት ወገኖችም የመጀመሪያ እርዳታ እየቀረበ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ካለው የምግብ እጥረት በተጨማሪ በተያዘው የፈረንጆ አመት የሕወሃት አገዛዝ መከሰቱን ያላመነበትና ምንም አይነት ጥንቃቄ ያልተደረገበት የኮሌራ ወረርሽኝ ወደ 800 የሚደርሱ ሰዎችን መግደሉንም ዘገባው አመልክቷል።
የጎርፍ አደጋው ከግጭቱ ጋር ተዳምሮ በሶማሌና በኦሮሞ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችን ስቃይ እንዳባባሰው ሪፖርቱ አክሎ ጠቅሷል።