እነ እስክንድር ነጋ በድጋሚ መታሰራቸው የስርአቱን አለመለወጥ ያሳያል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2010) ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣አንዱአለም አራጌ እና ተመስገን ደሳለኝኝን ጨምሮ 12 ታስረው የተለቀቁ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንደገና በቁጥጥር ስር መዋላቸው የአገዛዙን አለመለወጥ እንደሚያሳይ ተነገረ።

እነ እስክንድር ነጋ በተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት  ቤት በተካሄደ  ግብዣና የሽልማት ስነስርአት  ላይ እያሉ ትናንት ዕሁድ በፖሊስ ታስረው ተወስደዋል።

የእስሩ መንስኤ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ለምን ያዛችሁ፡፣ ግብዣውስ እንዴት ያለፈቃድ ተካሄደ በሚል እንደሆነ ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ለቡ በሚገኘው በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ቤት ታስረው ለተፈቱ ጓደኞቹ ግብዣ እየተደረገ በነበረበት ጊዜ በፖሊስ ተከበው የታየዙት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በጠቅላላው 12 ናቸው።

እነሱም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዷለም አራጌ፣ ጦማሪ ዘላለም ወርቅ አገኘሁ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፣ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሀይሉ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ይደነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ተፈራ ተስፋየ፣ አዲሱ ጌታነህና መሆናቸው ታወቋል።

ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ምርመራ ያደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።

መርማሪዎቹ ለምን ተሰበሰባችሁ ፈቃድስ አላችሁ ወይ?የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ነው የተነገረው።

ዳቦ ተቆርሶ ፈንድሻ ተነስንሶ በአገር ባህል ልብስ ደምቀው በመዝናናት ላይ እያሉ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ለምን ሰቀላችሁ ተብለው በምርመራ ላይ የሚገኙት እነ እስክንድር ነጋ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አንዳቸውም አለመፈታታቸው ተገልጿል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና ዲሞክራሲን ለማጎልበት በሚል በቅርቡ በይቅርታ የተለቀቁት እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌና ተመስገን ደሳለኝ እንዲሁም ሌሎች 9 ታሳሪዎች እንደገና መታሰራቸው አገዛዙ አሁንም ለለወጥ ያልተዘጋጀና መሰሪ አካሄዱን እንደቀጠለበት ነው ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አስተያየታቸውን በማህበራዊ ደረገጽ ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል።