እነ አቶ በቀለ ገርባ  ለሕገወጡ ፍርድ ቤት ቃላችንን አንሰጥም አሉ

ነሃሴ  ፭ ( አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮሚያ ክልልን አመጽ ተከትሎ ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረው የሚንገላቱት  የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጄኔ ጣፋ፣አዲሱ ቡላላን ጨምሮ የመድረክ ፓርቲ አባል የነበሩት አቶ ጉርሜሳ አያኖ ዛሬ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ተከሳሾቹ በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡ ከፍርድ ቤቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የክስ መቃወሚያቸውን አሰምተዋል።

አቶ በቀለ ገርባ ”ፍርድ ቤቱ እዚህ ያቀረበን በተጻፈለት መሰረት ሊፈርድብን እንደሆነ እናውቃለን።  ፍርድ ቤቱ ታዞ እንደሚሰራ ከዚህ በፊትም ካለጥፋቴ ለስምንት ዓመታት ተፈርዶብኛል። እኔ በራሴ ሕይወት ችግሩ ደርሶብኝ አይቼዋለሁ። ስለዚህ ለዚህ ፍርድ ቤት ቃሌን አልሰጥም” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ”የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በግልፅ ህገመንግስቱን እያፈረሰ ያለ ተቋም ስለሆነ ለዚህ ፍርድ ቤት ቃሌን አልሰጥም። ከአሁን በኋላም ወደዚህ ፍርድ ቤትም መምጣት አልፈልግም። ውሳኔውም ግልጽ ስለሆነ ባለሁበት ሆኜ ይድረሰኝ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እኛ ላይ የተፈጠመዉን በደል እንዲያዉቅልን እፈልጋለሁ!” በማለት ድጋሜ መገኘት እንደማይፈልጉና ፍርዱን ለሕዝቡ መስጠታቸውን አሳውቀዋል።

የመድረክ ፓርቲ አባል የነበሩት አቶ ጉርሜሳ አያኖ በበኩላቸው ”ክሱ ግልፅ አልሆነልኝም። እኔ ፖለቲከኛ ስሆን የመድረክ ፓርቲ አባል ነኝ፡፡ የእኛ ፓርቲ ሕገመንግስቱን ተከትሎ የተቋቋመ ሕጋዊ ፓርቲ ነዉ፡፡ የተከሰስኩት ግን የኦነግ አባል ነህ ተብዬ ነዉ። እኔ እስከማዉቀዉ አንድ ሰዉ የሁለት ድርጅት አባል መሆን አይችልም፡፡ ይሄ ክስ መንግስት መሬቴን አሳልፌ አልሰጥም ያለዉን የኦሮሞን ሕዝብ በጅምላ አሸባሪ ብሎ እየከሰሰ ነዉ።  ስለዚህ ቃሌን ለዚህ ፍርድ ቤት አልሰጥም” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

አቶ አዲሱ ቡላላም ለቀረበባቸው ክስ ሲመልሱ ‘ ‘የቀረበብኝ ክስ በሙሉ ድርሰት ነው። እኔ የመድረክ ፓርቲ እንጂ የኦነግ አባል አይደለሁም። ለሕዝቤ ብዬ በአደረግኩት ነገር በሙሉ ደስተኛ ነኝ። የተመሰረተብኝ ክስ በኦሮሞ ላይ የተመሰረተ ክስ መሆኑን ሁሉም ሰዉ እንዲያዉቅልኝ እፈልጋለሁ። እኔ ለዚህ ፍትህ አልባ ፍ/ቤት ቃሌን መስጠት አልፈልግም ተመካክራችሁ ዉሳኔዉን ባለሁበት አድርሱኝ ብለዋል።