እነ አቶ ስብሀት ነጋ በተሳተፉበት የህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ስብሰባ ጋዜጠኞች እንዳይገኙ ተከለከሉ

ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው የኣለም አቀፍ የሠላምና ልማት ኢንስቲትዩት  ከፍሬድሪክ ኤበርት ፈውንዴሸን ጋር በመተባበር ትናንት (ጁን 14/2012)  በሒልተን ሆቴል በጠራው አህጉር አቀፍ የምክክር ስብሰባ ላይ ሕገወጥ የገንዘብ ፍሰት ዓለም አቀፋዊ ችግር ቢሆንም ከሰሃራ በታች ባሉ ዜጎቻቸውን በብድርና በዕርዳታ የሚያኖሩ አገራት ያለው ውጤት እጅግ አስከፊ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጽዋል፡፡

ከመክፈቻ ፕሮግራም ውጪ ያለው የውይይት ግዜ ለጋዜጠኞች ዝግ በተደረገው በዚሁ መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስና ለመፈጸም አቅሙ አላቸው ተብሎ በሚገመቱት የመንግስት ሥልጣን በያዙ ኃይሎች ከሕዝባቸው ዘርፈው በልዩ ልዩ

መንገዶች በውጪ አገር የሚያሰቀምጧቸው ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለንዋይ ለልማት በቀጥታ መዋል ቢችል ድህነትን በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረው እንደነበር ተነስቷል፡፡

አፍሪካ በወር ወደ 5 ቢሊየን ዶላር ብድርና ዕርዳታ እንደሚጎርፍላት ከዚህም ገንዘብ ውስጥ ጥቂት የማይባለው ለዘረፋ የተጋለጠ መሆኑ ተወስቷል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ የመወያያ ጥናት ያቀረቡት ሚስ ጋርቢስ ኮራጂያን የሙስና መንሰራፋት ለህገወጥ ገንዘብ ፍሰት መሰረት ነው፡፡ የሙስና መንሰራፋትም የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያቀጭጭ፣የሐብት ብክነትን ፣የፖለቲካ አለመረጋጋትን እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡

ብዙዎችን ለትዝብት የዳረገው ሙስና በአገሪቱ ቀዳሚ ማህበራዊ ችግር ቢሆንም ጋዜጠኞች እንዳይሳተፉ መደረጉ ነው። አለማቀፉ የፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ተቋም ባለፉት 8 አመታት  ከኢትዮጰያ ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ በህገወጥ መንገድ መውጣቱን ይፋ አድርጎ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትም ጉዳዩን ሳያስተባብል ቆይቶ አለማቀፍ ጫናው ሲበዛበት አብዛኛው ገንዘብ የሚወጣው በንግድ ሚዛን ጉድለት ነው በማለት በአቶ መለስ ዜናዊ አንደበት አስነግሮ ነበር። ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ በቅርቡ ባወጣው ሌላ ሪፖርት በኢትዮጵያ አብዛኛው ገንዘብ የሚወጣው በሙስና መሆኑን መጠቆሙ የአቶ መለስ መንግስትን አስደንግጦ፣ ካለፉት 2 ወራት ጀምሮ በሙስና ዙሪያ የተለያዩ ስብሰባዎች ተዘጋጅተዋል።

የአለማቀፍ ለጋሽ አገራት ሪፖርቱ እንዳስደነገጣቸው በተለያዩ መንገዶች ሲገልጡ እና በመለስ መንግስት ላይ ጫና ሲያሳድሩ ተስተውሏል። ትናንት በሂልተን ሆቴል የተደረገው ስብሰባም የአለማቀፉ ጫና ውጤት ነው ተብሎአል። ይሁን እንጅ አቶ ስብሀት ነጋን ጨምሮ ከላይ እስከታች ያሉት የኢህአዴግ ባለስልጣናት በሙስና እንደተዘፈቁ የሚታመን በመሆኑ፣ እንዲህ አይነት ጉባኤዎች ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ እንደማይታመን ዘጋቢአችን ገልጧል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ እንዳገኘች ይታመናል።

ባለፉት 8 አመታት ከአገሪቱ በሙስናና በተለያዩ ህገወጥ መንገዶች የወጣው ገንዘብ በዚህ አመት መንግስት ለአገሪቱ የአንድ አመት ወጪ ከመደበው በጀት ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ይበልጣል። ብዙዎች በሙስናው ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት የህወሀት ባለስልጣናት ናቸው በማለት ይጽፋሉ።

አፍሪካ እስካሁን ድረስ ከ1 ትሪሊየን 800 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር የተነሳ አጥታለች።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide