ሐምሌ ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ያሉት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት የሆኑት 14 ተከሳሾች፣ በ2007 ዓም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በመንግስት ወታደሮች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የፌደራሉ አቃቢ ህግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበው የክስ ዝርዝር ያመለክታል።
የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በሰሜን ጎንደር ለሚካሄዱ ጦርነቶች በአደባባይ እውቅና የማይሰጥ ቢሆንም፣ በታጋይ ወታደሮች ላይ የሚቀርቡት ክሶች ግን ጦርነቶች ስለመካሄዳቸው የሚያስረዱ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ተማረኩ የሚባሉ ወታደሮች ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች ሲቀርቡ፣ በሰላም እጃውን እንደሰጡ እንጅ እንደተዋጉ አይገለጽም።
በእነ ገብሬ ንጉሴ መዝገብ የተከሰሱት 14 ተከሳሾች፣ የአርበኞች ግንቦት7ትን አላማ በመደገፍ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ 22 ሆነው አለማየሁ መለስ በተባለ ታጋይ መሪነት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓም በቃፍታ ሁመራ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የክስ ዝርዝራቸው ያሳያል። ታጋዮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ክላሽ፣ 240 ጥይት፣ሁለት ሁለት ቦንብ፣ሶስት ሶስት የክላሽ ካዝና፣ ለየቡድኑ ደግሞ አንድ የጦር ሜዳ መነፀር፣ ሁለት ሁለት ሞባይል፣ 20 ሺህ ብር ፣ ፎቶ ካሜራና የቅስቀሳ ወረቀት እንደተሰጠና ያንን ይዘው በመግባት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓም ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ጋር ጦርነት ማድረጋቸውን ያትታል።
ልዩ ቦታው ማይሰገል ላይ በተደረገው ውጊያ ምክትል ኮማንደር ወልደሚካኤል ገ/ እግዚያብሄር ጭንቅላቱ ላይ፣ሚሊሻ ካህሳይ ሆዱ አካባቢ፣ መቶ አለቃ ሀጎስ ኪ/ ማርያም ደረቱ ላይ ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል። እንዲሁም ተከሳሾቹ አስር አለቃ ዘካሪያስ አብደላ አመዴን እጁ ላይ፣ አስር አለቃ አብዲ ሰይድን አፉ ላይ፣ ረዳት ሳጅን መሐሪ አበበን የቀኝ እጇ ላይ፣ ምክትል ሳጅን ገ/ ሚካኤል ገ/ ህይወትን ጭንቅላቱ፣ የግራ እጅ ጣቶቹና መቀመጫው ላይ፣ ረዳት ሳጅን መብራህቱ ገሰሰውን ሆዱ ላይ በመምታት ከባድ ጉዳት አድርሰዋል ሲል አቃቢ ህግ ይዘረዝራል።
ክሱ በማከልም ሰኔ 26፣ 2007 ዓም ደግሞ ፀገዴ ልዩ ቦታው ወርዒ ካዛ ወንዝ ላይ ከቀኑ 6 ሰዓት ተኩስ በመክፈት ሚሊሻ ገ/ ህይወት ተስፋየን በግራ ሽንጡና አንገቱ ላይ ፣ ሚሊሻ ጣዓመ ካህሳይን ግራ እግሩ ላይ፣ ሚሊሻ ሀ/ ማርያም ሀይሉን ቀኝና ግራ እግሩ ላይ፣ ሚሊሻ ታመነ አለሙን ቀኝ እግሩ ላይ፣ ሚሊሻ ገ/ ህይወት አብርሃ ቀኝ እጁ ላይ በሁለት ቦታ በመምታት ጉዳት አድርሰዋል ይላል።
በዚሁ ቀን የተደረገውን ጦርነት በተመለከተ ኢሳት በወቅቱ ዘገባ አቅርቦ ነበር።
ታጋዮቹ በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለው ለመጨረሻ ጊዜ ሲሆን፣ አቃቢ ህግ በመጀመሪያ አቅርቦ ያሰማው የ3 ሰዎች ድምጽ ከድምጽ መቅረጫው ላይ ጠፍቷል በመባሉ ፍርድ ቤቱ በድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ቢጠይቅም፣ ፖሊስ ምስክሮች ለእርሻ በረሃ ወርደዋል በማለት ረጅም ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። ተከሳሾቹ በበኩላቸው አቃቢ ህግ አቅርቦ ያሰማቸው ምስክሮች በበቂ ሁኔታ መመስከር ባለመቻላቸው ድምጹ ሆን ተብሎ እንዲጠፋ መደረጉን በመግለጽ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።