እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ 10 የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትንና 141 ሌሎች ሰዎችን ለምስክርነት እንዲቀርቡላቸው ጠየቁ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)

 ከወራት በፊት የግንቦት ሰባት ሃይልን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ አራት ተከሳሾች 10 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ 141 ሰዎችን በምስክርነት እንደቀረቧቸው ጠየቁ።

አቶ አባይ ፀሃኤ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ ተፈራ ዋልዋ ተከሳሾቹ ለምስክርነት እንዲያቀርቧቸው የጠየቋቸው ምስክሮች መሆናቸው ታውቋል።

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የነበሩት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ት እየሩሳሌም ተስፋውና አቶ ፍቅረማሪያም አስማማው እንዲሁም ተከሳሾቹን ድንበር እንዲሻገሩ በመምራት የተጠረጠረው አቶ ደሴ ካህሳይ ባለፈው አመት ወደ ኤርትራ ለማቅናት ሙከራ አድርጋችኋል ተብለው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።

ተከሳሾች  ድርጊቱን እንደፈጸሙ ለችሎት በማመን ሰላማዊ ትግልን በሃገር ውስጥ ማካሄድ ባለመቻላቸው ምክንያት እርምጃውን እንደወሰዱ አስታውቀዋል።

ጉዳዩ ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤቱም ተከሳሾችን ጥፋተኛ በማለት የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ከወራት በፊት ውሳኔ ሰጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ ተከሳሾች ክሳቸውን ለመከላከል ይረዳ ዘንድ 141 ሰዎች በምስክርነት እንዲቀቡላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ወደ 10 የሚጠጉትም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መሆናቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ ሃጎስና እንዲሁም ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌና ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት የጥሪ ወረቀቱ በፍርድ ቤቱ በኩል እንደሰጥላቸው ተከሳሾቹ ጥያቄን እንዳቀረቡ ታውቋል።

ጉዳዩን በመመልከት ላይ ያለው ፍ/ቤቱም ለሚያዚያ 28, 2008 ተለዋጭ ቀጠሮን ሰጥቷል።