እስካሁን 1.2 ቢሊዮን የጨረሰው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ለማለቅ ተጨማሪ ብድር ያስፈልገዋል ተባለ

ኢሳት ዜና (ነሐሴ 21 ፣ 2007)

ግንባታው ለ 12 አመታት ያህል ሲካሄድ የቆየውና የእዳ መጠኑ 1.2 ቢሊዮን ብር አካባቢ የደረሰው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተጨማሪ ብድር ካልጸደቀለት በስተቀር ስራውን በተያዘለት እቅድ መሰረት እንደማይጀምር ምንጮት ለኢሳት ገለጡ።

መንግስት የተንዳሆ የስኳር ልማት ፕሮዳክሽን በአምስት አመት የልማት እቅድ መሰረት ወደማምረት ደረጃ ለማሳደግ ቢጥርም ግንባታው በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ሊያልቅ አለመቻሉን የልማት ባንክ ምንጮች ገልጸዋል።

የህንዱ ኩባንያ ስራውን እንዲጀምር በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ገነት ዘውዴ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን የተናገሩት ምንጮች፣ ኩባንያው በቂ አቅም ሳይኖረው በጉቦ ስራውን እንዲረከብ መደረጉን አስረድተዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ የ 30 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ማፅደቃቸው የሚታወቅ ሲሆን በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ግርማ ብሩ ከፕሮጀክቱ ጋር ንክኪ እንዳልነበራቸው የልማት ባንክ ምንጮች ገልጸዋል።

የከተማና ልማት ኮንስትራክሽን ምክትል ሚኒስትር የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ ለስኳር ፋብሪካው ግንባታ ለሰራተኞች መኖሪያ ቤትና ለሌሎች ስራዎች የሲሚንቶና የብረታ ብረት አቅርቦቱን ስራ እንዲመሩ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበረም ታውቋል።

ይሁንና ሚኒስትሩ ከንግድ ሸሪኮቻቸው እንዲሁም ከመንድማቸው አቶ ጌታቸው እቁባይ ጋር በመሆን የተገዙ በርካታ ቶን ሲሚንቶዎችና ብረታ ብረቶችን ከፍተኛ የኢምፖርት ዋጋ ማቅረባቸውን ምንጮች አስረድተዋል።

ከዚሁ ድርጊት ጋር በተገናኘም አቶ ጌታቸው እቁባይና ሌሎች ግብረ-አበሮቻቸው ለእስር ተዳርገው እንደነበር ያወሱት እነዚሁ ምንጮች ሚኒስትሩ አቶ አርከበ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሃላፊነታቸው እንዲዛወሩ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።

ከሙስና ጋር በተያያዘ የስኳር ፕሮጄክቱ የዘገየ ቢሆንም አሁን ተጨማሪ ብድር ካልፀደቀ ፕሮጄክቱ በተያዘለት እቅድ ስራውን ሊጀምር ኣንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለኢሳት ገልጸዋል።