ኢሳት (የካቲት 17, 2008)
ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት እስራዔል በአደራዳሪነት እንድትሳተፍ የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት በማግባባት ላይ መሆናቸውን የሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ ሃሙስ ዘገበ።
የሃገሪቱ የፓርላማ አባል የሆኑትና የግብፅ አል-ፋርን የቴለቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆኑት ቶውፊክ አካሻ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ለመምከር ካይሮ ከሚገኙት የእስራዔል አምባሳደር ቼም ኮረን ጋር ቀጠሮ መያዛቸው ተገልጿል።
እስራኤል በአደራዳሪነት መሳተፏ ከፍተኛ ጠቅሜታ ያለው በመሆኑ ሃገሪቱን በጉዳዩ ዙሪያ ለማሳተፍ ምክክር ይካሄዳል ሲሉ የግብፅ የፓርላማ አባላት አስታውቀዋል።
የፓርላማ አባሉ ከዚህ ቀደም እስራዔል በአደራዳሪነቱ የምትሳተፍ ከሆነ ሁለት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜርት ውሃ ይሰጣታል ሲሉ መግለጻቸውን ጋዜጣው በዘገባው አውስቷል።
ይሁንና፣ የቀረበላቸው ጥያቄ ቀድሞ ህዝብ እንዲያውቀው መደረጉ እንዳስገረማቸው የተናገሩት የእስራዔሉ አምባሳደር ሃይም ኮረን የግብፁ የፓርላማ አባል ለሁለቱም ሃገራት ይጠቅማል ያሉትን ሃሳብ እንደሚቀበሉት ለየሩሳለም ፖስት ጋዜጣ አስረድተዋል።
የፓርላማው አባል ቶፊክ ኦካሻ፣ እስራዔል በአደራዳሪነት እንድትሳተፍ የሚመክረው የሁለቱ ወገኖች ውይይት በቀጣዩ ሳምንት እንደሚካሄድ ይፋ አድርጓል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ምክክር ተከትሎም እስራዔል ጥያቄውን ስለመቀበሏ አሊያም ስላለመቀበሏ ምላሽን የሚጠበቅ ሲሆን፣ የእስራኤል መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።
እስራኤል ከግብፅና ኢትዮጵያ ጋር መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት ይነገራል።
ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመቅረፍ ለሶስት አመት ያህል ጊዜ ድርድርን ቢያካሄዱም መግባባት ላይ መድረስ አለመቻላቸው የታወቃል።
ይህንኑ አለመግባባት ለመፍታትም ሁለቱ ሃገራት ሁለት የፈረንሳይ ድርጅቶችን በመቅጠር ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት (በተለይ በግብፅ) ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማስጠናት ስምምነት ያደረጉ ሲሆን ኩባንያዎቹ በቅርቡ ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።