እስረኞች ግፍና በደል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ አንድነት ፓርቲ አስታወቀ

ሰኔ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአውስትራሊያ እንደዘገበው  “በቃሊቲ እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙ የህሊና እስረኞች ደህንነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ በደሎች እየተፈጸሙባቸው ነው፡፡” ሲል የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ ላይ ያወጣውን መግለጫ በመጥቀስ ዘግቧል

 

በእሥር ቤቱ ፖሊሶችና ኃላፊዎች ሳይቀር ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ ዘለፋዎችና አሰቃቂ ድብደባዎች እንደሚፈፀምባቸው የገለፀው  አንድነት በመግለጫው ላይ በዝርዝር እንዳብራራው፣ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሆን ብሎ በማንጓተት፣ ሌሎች ወንጀል ፈፅመው ከታሰሩ ወንጀለኞች ጋር በማሰር፣ በጓደኞቻቸው፤ በዘመድ ወዳጆቻቸው፤ በሃይማኖትም ሆነ በሕግ አማካሪዎቻቸው የመጎብኘት መብታቸውን በመገደብ፣ ሲታመሙ በቂ ሕክምና እንዳያገኙ ፣ እንዲሁም እንደ ሌሎቹ እስረኞች የቀለም ትምህርት እንዳይከታተሉ በማድረግ፣ ራድዮ እንዳይሰሙም ሆነ ጋዜጦችን እንዳያነቡ በመከልከል ያለአግባብ መብታቸው ተጥሶ ከፍተኛ በደልና እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቋል።

ይህም ከልክ በላይ ሆኖ ያንገሸገሻቸው የሕሊና እስረኞች፤ አቤቱታቸውን  በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ አቤት ቢሉም ሰሚ በማጣታቸው፣  አንዳንዶቹ ከሰኔ 6 እስከ ሰኔ 9፤ 2004 ዓ. ም የዘለቀ የሦስት ቀን የረሃብ አድማ አድርገው እንደ  ነበር የጠቆመው ይኸው የአንድነት መግለጫ …. የህሊና እስረኞቹ አሁንም መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ  በረሃብ አድማው እንደሚቀጥሉበት መግለፃቸውን በማስታወቅ፤ በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ ካሁኑ መድከም መጀመራቸው እንዳሳሰበው እንደሆነ ገልጿል።

መንግስት የዜጎቹ ህይወትና ደህንነትን በተመለከተ የሚወስደውን ሃላፊነት የጎደለውን አካሄድ የኢትዮጵያ ህዝብ በትኩረት በመከታተል በመንግስት ላይ አሰፈላጊውን ጫና ማድረግ ይኖርበታል” ሲል ያሳሰበው አንድነት  በተለይም የሃይማኖት መሪዎች፤ አለም አቀፍ የቀይመስቀል ማሕበር እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የእነዚህን ውድ ኢትዮጵያዊያን ህይወት ለመታደግ የተለየ ጥረት ማድረግ፤ እንዲሁም የዓለም ማህበረሰብ ይህንን በሕግ ጥላ ስር በሚገኙት እስረኞች ላይ እየተፈፀመባቸው ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በትኩረት ተከታትሎ የገዥዎቻችን ባህሪ ማወቅና ከሰላማዊ ታጋዮች ጎን መቆም ይጠበቅበታል፤” ሲል ጥሪውን አሰምቷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide