እስረኞች ከፍተኛ ማሰቃየት እየተፈጸመባቸው ነው

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 26/2010)

በፖለቲካ ምክንያት ታስረው በወህኒ ቤት የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ ማሰቃየት እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ።

ከጊዜያዊ ህመም እስከ ዘላቂ የአካል ጉዳት የደረሰ ቅጣት እንደሚፈጸምባቸውም እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የሚፈጸሙና አሰቃቂ የሚባሉት ድርጊቶች ችሎት ፊት ሲቀርቡ ምናልባትም የህግ ባለሙያዎች መቀለጃ ወይንም የበለጠ ቅጣትን ማክበጃ ተደርገው ይወሰዳሉ።

እንዲህ አይነቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው ደግሞ ምንም አይነት ወንጀል በሌለባቸው፣ወንጀል ሰርተው እንኳን ቢሆን ህጉ እንደ ህግ ብይን ሳይሰጣቸው በእስር ቤት እንዲሰቃዩ በተደረጉ ዜጎች ላይ ነው።ለእስረኞቹ የተለያየ ስም ይሰጣቸዋል።የማሰቃያ መንገድም ይቀመጥላቸዋል።

በእነ ሚፍታህ ሸህ ሱሩር የክስ መዝገብ 74ኛ ተከሳሽ የሆነው ፈረደ ክንድሻቶ ይርጋም ከነዚህ አንዱ ነው።

ፈረደ ዛሬ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ጋር በተያያዘ ሱሪ እንኳን መልበስ አይችልም።በደረሰበት የከፋ ድብደባ ምክንያትም በትክክል መራመድ አይችልም።

ዳንሻ ድረስ ተወስዶ ተደብድቧል፣ወደ ትግራይ ተግዞ በገመድ ግንድ ላይ ታስሮ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል።

በጉድጓድ ውስጥ እያለ ለፈረደ ምግብና ውሃን ያቀመሰው አልነበረም።

በሁመራ እጁ የኋሊት ታስሮ ጸሃይ ላይ እንዲሰጣ ተደርጓል።በድብደባው ብልቱና ሆዱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ፈረደ ወደ ሆስፒታል ሳይሄድ ለረጅም ጊዜ ከነስቃዩ በእስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።

የኦፌኮ አባሉ አቶ ዴቢሳ በየነም የእስር ቤት ስቃይ ሰለባ ከሆኑት መካከል ናቸው።

በሙያቸው መምህር የሆኑት አቶ ዴቢሳ በሽብር ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

አቶ ዴቢሳ በደረሰባቸው ስቃይ በአግባቡ መራመድ እንዳይችሉ እንኳን ተደርገዋል።

በሽብር ተግባር የተከሰሰችው ንግስት ይርጋ በእስር ቤት አይምሮዋን እስክትስት ተደብድባለች።

9 የእግር ጣቶቿ ጥፍሮች በጉጠት ተነቅለዋል፣ በየጊዜው የከፋ ድብደባ ተፈጽሞባታል።ይሄ ሁሉ ስቃይ ሲደርስባት ግን ለጉዳቷ ህክምና እንድታገኝ ወደ ሆስፒታል የወሰዳት አልነበርም።–እዛው ያሉ እስረኞች ናቸው ደሟን የጠረጉላት ቁስሏን ያከሟት።

ንግስት ይርጋ በፍትህ እጦት ለተሰቃየችውና የኦነግ አባል በሚል ለታሰረችው የእስር ቤት ጓደኛዋ በችሎት ፊት ቀርባ በእስር ቤት ይደርስባት የነበረውን ስቃይ በዝርዝር በማስቀመጥ ምስክርነቷን ሰጥታለች።–ምስክርነቷ ደግሞ እጅግ የከፋውን የእስር ቤት ገጽታ የሚያሳይ ነበር።

ከችሎቱ ስትወጣ ከፊት ለፊቷ በደረሰበት ድብደባ እግሩን እየጎተተ የሚራመደውን ፈረደ ክንድሻቶን ስታይ እምባዋን መቆጣጠር ያልቻለችው ንግስት እረ የወገን ያለ እረ የፍትህ ያለ ስትል ፊቷን እያጠበ በሚወርደው እምባዋ ተማጽናለች።

በእስር ቤት እንድንበላ የምንደረገው የተፈጨ አሸዋ ነው ሲል የከፋውን የእስር ቤት ኑሮ በአደባባይ የተናገረውን ባንተወሰን አበበን ጨምሮ በየዕለቱ በችሎት በመቅረብ አሳዛኝ የሆነውን የእስር ቤት ኑሯቸውን የሚናገሩትን ዜጎችን ቁጥር ሕዝብ ይናገር ይላሉ የአይን እማኞች።

የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው አሁን የህወሃት አገዛዝ እያደረገ ካለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ በእስር ቤት የሚታጎሩትንና ለከፋ ስቃይ የተዳረጉትን ዜጎች ቁጥር መናገር አይቻልም ይላሉ።

ምክንያቱም የህወሃት አገዛዝ በሰበብ አስባቡ በግፍ እያፈሰ እስር ቤት የሚያጉራቸው ዜጎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ መምጣትና በህወሃት ፖለቲካ የሚቃኙት ፍርድ ቤቶችም የፍትህ ስርአቱን ከማስፈጸም ይልቅ የዜጎች ስቃይን የሚያባብሱ በመሆናቸው ያለፍትህ በእስር ቤት የሚሰቃዩት ዜጎች ቁጥር የከፋ ሆኗል።