(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 14/2010)በኢትዮጵያ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አስቸኳይ እርዳታዎች የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከ16 ሚሊየን በላይ መድረሱን ለኢሳት የደረሰው የመንግስት ሰነድ አመለከተ።
እስከ ታህሳስ 2011 ድረስ ይህ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉት ውስጥ ከ6 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ናቸው ።
ከሶማሌ ክልል ነዋሪዎች 80 በመቶው አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ናቸው ።
የኢትዮጵያ መንግስትና ከ80 በላይ እርዳታ ሰጪ ሃገራትና ተቋማት በጋራ ባዘጋጁት የ2018 እቅድ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ብዛት ከ16 ሚሊየን በላይ መሆናቸው ተመላክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 7 ነጥብ 9 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን የመጠጥ፣ ውሃና መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ምግብ ነክ ያልሆነ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 8 ነጥብ 9 ሚሊየን መሆኑን ሰነዱ ይገልጻል።
ይህ ለኢሳት የደረሰው ባለ 54 ገጽ ሰነድ ላይ እስከ ታህሳስ 2011 ድረስ አስቸኳይ እርዳታውን ለማድረግ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
በብሔራዊ አደጋ አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ፊርማ ለእርዳታ ሰጪ ተቋማትና ሃገራት በተበተነው በዚህ እቅድ ላይ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ግጭትና በአስከፊ የአየር ለውጥ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አመላክቷል።
እስከ ታህሳስ 2011 ድረስ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከተገለጹት 16 ሚሊየን ዜጎች ውስጥ 6 ሚሊየን ያህሉ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ መሆኑን ሰነዱ አመላክቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ተብሎ ከተገለጸው የሶማሊያ ክልል ነዋሪ ውስጥ 80 በመቶው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ እርዳታ የሚያስፈልገው ነው።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ በቅርቡ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት የሚያስጎመዥ ደረጃ መድረሱን መግለጹ የሚታወስ ነው።