ሰኔ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ቆጠራ ኮምሽን በ1999/2000 ዓ.ም የሶስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ
ውጤት ይፋ በተደረገበት ወቅት በተለይ የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከትንበያው ዝቅ
ብሎ ተገኝቷል በሚል በቀድሞ የፓርላማ አባላት በቀረበው ቅሬታ ላይ ኮምሽኑ ፍተሻዎችን ማድረጉንና ምንም ዓይነት
ስህተት አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የቤቶች ቆጠራ ኮምሽን ዛሬ ለፓርላማው ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው ህዳር 25 ቀን 2001 ዓ.ም የሶስተኛውን
የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ለፓርላማው ባቀረበበት ወቅት ባልተለመደ መልኩ የቀድሞ የኢህአዴግ የፓርላማ አባላት
የአማራ ሕዝብ ቁጥር አንሷል የሚል ጠንካራ አቤቱታና ነቀፌታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ኮሚሽኑ ከዓለምአቀፍና ከአገር ውስጥ በተውጣጡ የቴክኒክ አማካሪዎች በመታገዘ የቆጠራው አፈጻጸም ላይ ጭምር ቴክኒካዊ ጥናቶችን ሲያደርግ መቆየቱን፣ በተካሄደው ፍተሻ የአማራን ሕዝብ ብዛት በተለየ መልኩ ሊያስቀንስ የሚችል ሁኔታዎች
አለመኖራቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረትም ድጋሚ ቆጠራ ማካሄድ እና ማስተካከያ ማድረግ አያስፈልግም ብሎአል፡፡
በወቅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው 73 ነጥብ 3 ሚሊየን ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ 17 ሚሊየን 115 ሺህ 905 ያህሉ የአማራ ሕዝብ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህም ሆኖ ኮምሽኑ የአራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከአስር ዓመታት በኋላ ከመካሄዱ አስቀድሞ በመካከል ሰፋ ያለ
ናሙና በመውሰድ ኢንተር ሴንስዋል ሰርቬይ (Inter censual survey) ጥናት በ2004 ዓ.ም ከመንግስትና ከተባበሩት
መንግስታት የስነሕዝብ ፈንድ በተገኘ 73 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መሰረታዊ የሆኑ የስነሕዝብ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ሁኔታዎችን አመልካቾችን ለማግኘት አቅዶ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ይህ ጥናት በመላው ዓለም የተለመደ ከመሆኑም በላይ የአማራ ክልል ሕዝብ ቁጥር ከትንበያው ለማነሱ ተጨማሪ መረጃ ሊያስገኝ እንደሚችል በማመን፣ በተጨማሪም በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የአዲስአበባ ሕዝብ ብዛት ቁጥሩ አንሷል የሚል ግምት መኖሩ
በተለያየ አጋጣሚዎች ሲገለጽ በመቆየቱ የኮምሽኑ ጽ/ቤት ልክ እንደአማራ ክልል ሁሉ ለአዲስአበባ ከተማ አስተዳደርም ሰፋ ያለ ናሙና በመውሰድ ጥናቱ እንዲካሄድ ማድረጉን ጠቅሷል፡፡
የኢንተር ሴንስዋል ሰርቬይ የስነሕዝብ ጥናት በአማራ ክልል በ4 ሺ 322፣በአዲስአበባ በ7 ሺ 576 ፣በሶማሌ ክልል በ7 ሺ 826 የቆጠራ ቦታዎች በሚገኙ ለናሙና በተመረጡ ቤተሰቦች ላይ አምና ተካሂዶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በ1999 ዓ.ም 73 ነጥብ
3 ሚሊየን የነበረው በ2004 ዓ.ም ወደ 82 ነጥብ 6 ከፍ ማለቱን፣ የአማራ ሕዝብ ቁጥር ከ17 ሚለዮን 100ሺ
ወደ 19 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ማደጉን የአዲስአበባ ሕዝብ ከ2 ሚሊዮን 6 መቶ ሺ ወደ 2 ሚሊዮን 9 መቶ ሺ ማደጉን መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ኮምሽኑ ይህን ይበል እንጂ የአዲስአበባ ማስተር ፕላን ጥናት ጽ/ቤት የአዲስአበባንና ዙሪያዋን ህዝብ ቁጥር
እስከ 5 ሚሊየን በማድረስ እየሰራበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ኮሚሽኑ በጥናቱ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉትን የኢትዮጵያ ምሁራን እና የውጭ ድርጅቶችን በደፈናው ከመግለጽ በስተቀር ዘርዝሮ አላቀረበም። ኢህአዴግ ሆን ብሎ የአማራውንና የአዲስ አበባን ህዝብ ቁጥር አሳንሶአል በሚል ከፍተኛ ትችት ሲደርስበት እንደነበር ይታወቃል። በኮሚሽኑ የቀረበው መልስ ብዙዎችን ያሳምን አያሳምን ለወደፊቱ የሚታይ ይሆናል በማለት ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።