የካቲት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ፦” ውሸት ቢደጋገምም፤ እውነትን ሊቀብር አይችልም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ የህወሀት አገዛዝ እንደተለመደው ኤርትራን ለማጠልሸት ኋላ ቀርና ርካሽ ፕሮፓጋንዳ መንዛቱን በመጥቀስ፤ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዓላማውም እውነታውን ለመደበቅና ከውስጥ እያየለ የመጣበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ውጫዊ ለማስመሰል እንደሆነ ገልጿል።
የኤርትራ ህዝብና መንግስት የዚህ ዓይነት ተደጋጋሚ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየተነዛባቸው ባለበትና መሬታቸው በኃይል በተያዘበት ሁኔታ ትኩረታቸውን ልማት ላይ ማድረጋቸው በደንብ የታወቀ ነው ያለው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር፤ ለእንዲህ ያለ አጀንዳን ለማጣጣም ቀርቶ ለመስማት “ፍላጎት” የላቸውም ብሏል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በባህላዊ ወርቅ ማምረት ሥራ ላይ የነበሩ ሰማንያ አምስት ሰዎች በኤርትራ እንደተጠለፉባት በመግለጽ፤ ዜጎቿ ካልተለቀቁ በኤርትራ ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ይህ የማስጠንቀቂያ መግለጫ ውሎ ሳያድር የታገቱት ዜጎች መለቀቃቸውን የገለጸው ኢህአዴግ፤ ሰዎቹ የተለቀቁት የሱዳን መንግስት -በኤርትራ ላይ ግፊት አድርጎበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል።
ይህ የኢሃዴግ “ታገቱ፤ተለቀቁ” መግለጫ በፍጥነት መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ተለቀዋል ፣ ለመባሉ የተሰጠው ምክንያት በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያንን ፈገግ አሰኝቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ ያልተዋጠላቸው በርካቶች የሰጡት አስተያዬት ፦” መግለጫው ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰውን አመጽ ለማስቀየስ የወጣ ነው” የሚል ነው።
የህወሀት አገዛዝ ሥልጣኑን ለማስቀጠልና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ተቆጣጥሮ ለመዝለቅ የኢትዮጵያ ህዝብን እየከፋፈለ ነው ያለው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ውስጥ የመገንጠል መብት እንዲካተት የተደረገውም አገዛዙ ሲወድቅ ተግባራዊ እንዲያደርገው በማሰብ እንደሆነ ያትታል።
መግለጫው በመጨረሻም የኤርትራ መንግስት የተባለውን ነገር የመጸም ምንም ዓይነት ሀሳብ እንደሌለውና ለእንዲህ ያለ ፕሮፓጋንዳም የሚያባክነው ጊዜ እንደሌለ በመጥቀስ፤ መግለጫው ከህወሀት አገዛዝ ጀርባ ያለውን ተደጋጋሚ ውሸት ያጋለጠ ነው ብሏል።