ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ኢትዮጵያ በቅርቡ በኤርትራ ላይ ለሰነዘረችው ጥቃትም ሆነ በአካባቢው ላሰማራችው ሳራዊት የአሜሪካ እጅ አለበት። የአሜሪካ መንግስት ሁለቱም ሃይሎች ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ ያስጠነቀቀ ቢሆንም፣ የኤርትራ መንግስት የአሜሪካ መግለጫ ጎጂውንና ተጎጂውን እኩል የሚፈርጅ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሎአል።
የኤርትራ መንግስት በሰሞኑ ግጭት የአሜሪካ እጅ አለበት ቢልም ዝርዝር መግለጫ ወደ ፊት እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም። በኤርትራ እና በአውሮፓ መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ቢታይበትም፣ በኤርትራ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ግን እስካሁን መሻሻል አላሳዬም። የኤርትራ መንግስት፣ የአሜሪካ መንግስት ለኢህአዴግ መንግስት ጭፍን ድጋፍ ይሰጣል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርብ ይሰማል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው አመት አሜሪካ መንግስት ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚጠጋ ወታደራዊ ድጋፍ ለኢህአዴግ መንግስት አድርጓል። የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር የሚያደርገውን ጦርነት አሜሪካ በገንዘብ እና በማቴራል እንደምትደግፍ ዘገባዎች ያሳያሉ።
በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አሁንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚታዩ ሲሆን፣ ሁለቱም አገራት ወደ ሙሉ ጦርነት ሊገኑ ይችላሉ በማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎችም ዲፕሎማቶች እያስጠነቀቁ ነው። ሰሞኑን በተደረገው ግጭት ኤርትራ 200 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግዷልን ማስታወቋ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በኤርትራ በኩል ስላደረሰቸው ጉዳት እስካሁን የገለጸቸው ነገር የለም።