(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/2011) በድንበር ውዝግብ ለዓመታት በባላንጣነት የቆዩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያዝ አፈወርቂና የጅቡቲው መሪ ኢስማኤል ኡማር ጊሌህ ተገናኝተው በጋራ ጉዳያቸው ላይ መከሩ።
ሳውዲ አረቢያ ሪያድ ውስጥ የተገናኙት ሁለቱ መሪዎች አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመጀመርና ጉርብትናቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ገለጹ።
ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረመስቀል በቲውተር ገጻቸው እንደረገጹት ሁለቱ መሪዎች ስምምነቱን የፈረሙት በሳውዲ አረቢያ ውስጥ ነው።
ሁለቱም መሪዎች ይህ አዲስ ምዕራፍ እንዲጀመር ጥረት ላደረጉት የሳውዲው ንጉስ ሳልማንና ለአልጋወራሹ መሐመድ ቢን ሳልማን ምስጋና ማቅረባቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ በአካባቢው ሃገራት ትብብሮች ቀጥለዋል።
የሶማሊያ ኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች አስመራ ላይ የጋራ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ የሶስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ጊሌህ ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ የ20 አመቱን የድንበር ውዝግብ ቋጭተው የሰላም ጉዞ በመጀመራቸው የሳውዲው ንጉስ ለሁለቱ ሃገራት መሪዎች የሃገራቱን ከፍተኛ ሜዳሊያ ሰጥተዋል።