ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በየአመቱ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል፤ በመላው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ድምቀትና በከፍተኛ ተቃውሞ ተከብሮ ዋለ። በደሴ አዲስ አበባ፤ ናዝሬትና ሌሎች ከተሞችም ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበር ታውቋል።
ከኢትዮጵያ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከሰላት በፊትም በኋላም ቢጫ ካርዶችና መፈክሮች በብዛት ይውለበለቡ ስለነበር፤ ቢጫ-የለሽ ምስል ያጣው ኢቲቪ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ፤ በዝግጅቶቹ ብሄራዊ በዓሉን ሳይጠቅስ እንደዋለ ታውቋል።
በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተገኙ ሙስሊሞች ቢጫ ወረቀቶችንና ጨርቆችን በማውለብለብ እንዲሁም መፈክሮች በመያዝና በማሰማት፤ ላለፈው ምርጫ ያላቸውን ተቃውሞና የመንግስትን ጣልቃገብነት፤ እንዲሁም የታሰሩ አመራሮች እንዲፈቱ በመጠየቅ በከፍተኛ ጩኸት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደዋሉ፤ ከስፍራው የደረሱን ምስሎችና መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ አበባ ስቴዲየም።
በአዲስ አበባ በኢቲቪ በኩል የሚያልፉ አያሌ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ኢቲቪ ሌባ፤ ኢቲቪ አሸባሪ ሲሉ ተሰምተዋል።
አዲስ አበባ ኢቲቪ አካባቢ።
በተለይም በአዲስ አበባ በስቴዲየምና በሌሎች ስፍራዎች ከፍተኛ የፌደራል ሀይል ስምሪት እንደነበርና ወደስቴዲየም ለመግባት አራት ግዜ እንደተፈተሸ ከስፍራው ያነጋገርነው ምንጭ ጠቅሷል።
አንዳንዶቹ ፖሊሶች ተቃውሞ ከምርጫው በኋላ አይኖርም ተብለው እንደተነገራቸውና አሁንም በሚያዩት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደተደነቁ አልሸሸጉም።
ሕዝበ ሙስሊሙ “ፖሊስ የህዝብ ነው፤ ፌዳራል ፖሊስ ግን አሸባሪ ነው” የሚል መፈክር ያሰማ እንደነበርም ታውቋል።
በደሴ መስጊድም ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበር ታውቋል።
ደሴ።
በሁሉም ስፍራዎች በነበሩት የበአል አከባበር የተለመዱት የመንግስት ባለስልጣናትና የመጅሊስ ሰዎች ንግግሮች እንዳልተደረጉ ታውቋል። በአዲስ አበባ ስቴዲየም የነበሩ ምንጭ እንደጠቀሱት፤ ንግግር የማድረግ ሙከራ ሲደረግ፤ ዋ ዋ በሚል ጩኸት ንግግራቸው እንደተደናቀፈ ታውቋል።
በአዲስ አበባ ስቴዲየም፤ የመጅሊስ አመራሮች በከፍተኛ የፖሊስ አጀብ በመድረክ አካባቢ እንደታዩም ከስፍራው ለማወቅ ችለናል።
በሌላ ዜና፤ባለፈው እሁድ በደሴ በተፈጠረው ተቃውም በፖሊስ ተመተው ቆስለው ሆስፒታል ከገቡት ቁስለኞች ውስጥ፤ ፖሊስ ሻል ሻል ያላቸውን እየመረጠ ወደእስር ቤት እየወሰደ እንደሆነ የደሴ ምንጫችን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ገንዘብ በማሰባበስ በሆስፒታል የተኙትን ለመጠየቅ ቢሄድም፤ ፖሊስ ህዝቡ ቁስለኞቹን እንዳይጠይቅ እንደከለከለ ታውቋል።