ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 19/2010) የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው የተገኙት በመስቀል በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው መረጃ ደግሞ ኢንጂነር ስመኘው የሞቱት በጥይት ተመተው ነው።

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አዲስ አበባ A 29ሺ 722 በሆነው ቶዬታ ላንድ ክሩዘር መኪና ውስጥ በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ አካባቢ መኪናቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት የኢንጂነር ስመኘው ሕልፈት አነጋጋሪ ሆኗል።

የኢንጂነር ስመኘው ድንገተኛ ህልፈት ያስቆጣቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ድረስ በመሔድ የሞታቸው መንስኤ ተጣርቶ አስቸኳይ ምላሽ ለሕዝብ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን በምስል ተደግፎ ከተሰራጨው ዜና መረዳት ተችሏል።ኢንጂነር ስመኘው በቀለ  በጥይት ተመተው መገደላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል  ገልጸዋል።በቀኝ እጃቸው ሽጉጥ መገኘቱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኤሊክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ወስጥ ለ 32 ዓመታት ያገለገሉት የ53 ዓመቱ ኢንጂነር ስመኘው በቀለን ሞት ዋሽንግተን ሲደርሱ የሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሁኔታው መደንገጣቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት  ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢንጂነር ስመኘው ቤተሰብ እና ለኢትዮጵያም ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የለውጥ ሒደቱን ለማወክ ተከታታይ የሁከት ርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸው ሲጠቀስ ቆይቷል።

በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የብሔረሰብ ግጭት ከመቀስቀስ ጀምሮ በግለሰቦች ላይ የተነጣጠሩ ግድያዎች ተፈጽመዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር የአፍሪካ ግንባር ቀደሙ ቢሊየነር የሚስተር ዳንጎቴ ንብርት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ካማር እንዲሁም ሹፌራቸውና ጸሃፊያቸው ከአዲስ አበባ 90 ኪሎ ሜትር   ሙገር አካባቢመገደላቸው ይታወሳል።ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ላይ የተነጣጠረ የቦንብ ጥቃት መድረሱ ይታወሳል።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦቻቸውን አስቀድመው ከሃገር ማስወጣታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ይህም የሆነው ከስጋት ጋር በተያያዘ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።ቤተሰቦቻቸው  ባለቤታቸውን ጨምሮ በካና ዳእንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል።