ጥር ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው ጥር ወር መግቢያ ጀምሮ የአየር ላይ ፎቶ እየተነሳ ያለው አካባቢ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ” ኢትዮጵያ መሬቱ የእኛ መሆኑን እውቅና ሰጥታለች” በማለት ለአልጀዚራ የተናገሩት አልፋሽጋ እየተባለ የሚጠራው ቦታ መሆኑ ታውቋል።
ትናንት ኢሳት የመረጃና ደህንነት ኢንፎረሜሽን ባለሙያ በማናገር በሰራው ዘገባ ላይ በአሁኑ ሰአት የአየር ላይ ፎቶ ለማንሳት ምልክቶችን መሬት ላይ የማስቀመጡ ስራ የሚከናወነው 365 ኪሜ ርዝመት ባለው ቦታ ላይ መሆኑን ቢዘግብም፣ ይህ ርቀት ግን የአየር ላይ ርቀትን የሚያመለክት እንጅ የመሬትን እርቀት የሚያመለክት ባለመሆኑ ማስተከከያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል። በመጀመሪያው ሂደት ድንበር የማካለሉ ሂዳት የሚከናወነው 725 ኪሜ ርዝመት ላይ ባለው መሬት ላይ ሲሆን፣ ይህም አካባቢ ሱዳን የኢትዮጵያ መንግስት የእኔ መሬት መሆኑን አምኖልኛል በማለት የገለጸችው አልፋሽጋ እየተባለ የሚጠራውን ለም መሬት የሚያካትት ነው።
አልፋሽጋ የሚባለው ቦታ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመለየቷ በፊት ከራስካሳር እስከ አትባራ የሚደርሰውን ቦታ ያካልል እንደነበር የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ የኢህአዴግ መንግስት ለማስረከብ እየተዘጋጀ ያለው ከሰቲት ወንዝ እስከ አትባራ ድረስ ያለውን 725 ኪሜ የሚደርስ ሰፊ መሬት ነው። አልፋሽጋ በደቡብ አጥባራ፣ በሰሜን ሰቲት ማሃል ላይ ባህረነጋሽ በተባለ ወንዝ የተከበበ በመሆኑ፣ መሬቱ ለእርሻ ስራ እጅግ ተስማሚ ነው።
በሁለተኛው ዙር መሬት የማካለል ስራ ከሁመራ ጫፍ እስከ ኤልሚ ወይም የሱዳን፣ ኬንያና ኢትዮጵያ መገናኛ ድንበር ድረስ እንደሚካሄድ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፋሽጋ ሱዳን መሆኑን ኢትዮጵያ ማረጋገጫ ሰጥታለች ቢሉም፣ በኢህአዴግ መንግስት በኩል እስካሁን ምንም አይነት ማስተባበያ አልተሰጠም። ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያምና ቃለአቀባዩ ጌታቸው ረዳ ከሱዳን ጋር ምንም አይነት የድንበር ማካለል ድርድር እየተካሄደ እንዳልሆነ ገልጸው ነበር። ሱዳኖች በበኩላቸው የሁለቱ አገራት የድንበር ኮሚቴ ስራውን በማጠቃለል ላይ መሆኑንና የመጀመሪያው ድንበር የመለየት ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
የኢህአዴግ መንግስት የድንበር ጉዳዩን ለህዝብ ለምን ግልጽ ማድረግ እንደተሳነው የታወቀ ነገር የለም። መሬቱን በድብቅ ለማስረከብ የሚደረገው ሂደት በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ያመጣል ተብሎ አይታመንም።
የአካባቢው ነዋሪዎች በእርሻ ማሳዎች ላይ የሚተከሉትን ምልክቶች በመንቀል ተቃውአቸውን እንዲገልጹ ባለሙያዎች ጥሪያቸውን በድጋሜ አቅርበዋል።