ኢንሳ በኢሳትና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

ጥቅምት ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሰሞኑን አሻሽሎ ያዘጋጀውና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት እንዲወያዩበት የተዘጋጀው  ሰነድ ለኢሳት የደረሰ ሲሆን፣ ሰነዱ የመንግስት የመረጃና የደህንነት መስሪያ ቤት ወይም ኢንሳ በኢሳት በአሜሪካ እና በጀርመን ድምጾች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ከመማጸን ጀምሮ መንግስት በሴቶች፣ በወጣቶችና በምሁራን ስም የሃይማኖት ማህበራትን እንዲቋቋሙ እገዛ እንዲደርግ፣ በሰርተፍኬትና በዲግሪ ደረጃ የሃይማኖት ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት እንዲቋቋሙ እገዛ እንዲያደርግ ይመክራል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጥቅምት 2007 ለኢህአዴግ የምክር ቤት አባላት ያዘጋጀው ሰነድ 16 ገጾች ሲኖሩት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተከፋፍሎ፣ ለመንግስት ህልውና ስጋት ደቅኗል ባለው የሃይማኖት አክራሪነት ዙሪያ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ይሰነዝራል።

ሰነዱ ወጣቱን ከስራ አጥነት ችግር መታደግ በሚለው ንኡስ ርእስ ስር ” በአገራችን በተለይ ከ97 ዓም ድህረ ምርጫ ቀውስ በመማር የወጣቱ የልማትና ተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳደርና የተሳትፎ ጥያቄዎች ለመመለስ ያደረግነውና ያልተሳካ ውጤት ያገኘነውም በመሰረቱ ለስራ አጥነትና ለተስፋ መቁረጥ የተጋለጠ ወጣት ሊኖርበት የሚችለውን ተጋላጭነት በመኖሩ ነው አሁንም ይህ ስጋት በተማረው እና መሬት በሌላው ወጣት ዘንድ በስፋት አለ። በዚህ ረገድ ባለፉት ሰባትና ስምንት አመታት እጅግ የሚያስመካ ስራ ሰርተናል ማለት አይቻልም። ” ይልና ” በገጠርም በከተማም የትምህርት እድልን በማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ በግብርናና ከግብርና ውጭ የሚከናወኑ የልማት እድሎችን በመፍጠርና በማስፋት የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል የመሬት እጥረት ከስደተኛ ወጣቱ ጋር ተዳብሎ ከፍተኛ የፖለቲካ ስጋት ነው ለዚህም እስካሁን በጥቃቅንና አነስተኛ የሰጠነው በቢልዮን የሚጠጋ ብር መመለስ አልተቻለም። ” ብሎአል።

ሰነዱ ” በሃገራችን የሚንቀሳቀሱ የሃይማኖት አክራሪ ቡድን መሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑንም” ይጠቅሳል። “በመላ አገሪቱ በቀጣይ ለፓርቲያችን አስቸጋሪ ሁኔታ እና ለአላስፈላጊ ውድቀት የሚዳርገው በክርስትናም ሆነ በእስልምና እምነት ላይ ያለው አክራሪነት ነው” የሚለው ሰነዱ” ሁለቱ ሃይማኖት እርስ በርስ የሚያደርጉት መገፋፋት ለፖለቲካው መሪነት አማራጭ እና ከእርምጃ መንግስትን የሚታደገው ሆኖ ይገኛል ” ብለአል።

በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ ሃይሎችን በቀጣይነት ማጋለጥና መሰረት ማሳጣት በሚልው ክፍል ደግሞ ” የመንግስትን እቅዶችና አፈጻጸም እንዲሁም በአፈጻጸም ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎችን የሚለከት መረጃ ለህዝቡ በፍጥነትና በግልጽ ማቅረብ እንደሚገባ” ይመክራል። የክልል እና የፌደራል ሚዲያዎችንም በይዘት ቁጥጥሩ ሊጠብቅ እንደሚገባ ከገለጸ በሁዋላ ” የጥፋት ሃይሎች የሚነዙዋቸውን የሃሰት ፈጠራዎች በሙሉ እየተከታተልንና ምላሽ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እየለየን በብቁ መልእክቶች መመከት ይገባል” ሲል ያስቀምጣል።

ኢሳት፣ ቪኦኤ፣ የጀርመን ድምጽ የሬዲዮ ስርዓቶች በኢንሳ ቁጥጥር ስር ማዋል ያስፈልጋል፣ የሚለው ሰነዱ እያንዳንዱን የፈጠራ ድርሰት በዝርዝር ማንሳትና ይህንኑ ለመመከት የሚያስችል መልዕክት ለመቅረጽ ከመሞከር ተቆጥበን በየወቅቱ በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወገኖች የሚያነሷቸውን ነጥቦች መነሻ በማድረግ ጠንካራ የምከታ ስራ መስራት ተገቢ ነው ብለአል። በተለይ በሀገር ውስጥ ያሉ አባሎቻቸው ላይ የማያቆራርጥ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው ሲል ይመክራል።

የሃይማኖት ተቋማትን መደገፍ በመደገፍ በተናጠልና በጋር የውስጥ ተጋላጭነታቸውን እንዲያስወግዱ ማበረታታት በሚለው ተራ ቁጥር አንድ ስድስት ላይ ደግሞ ” ሃይማኖታዊ የወጣት፣ የሴቶች፣ የምሁራን አደረጃጀቶች ተፈጥረው ራሳቸውንና ሌላውን ተከታይ በተደራጀ ሁኔታ የተሟላ ሃይማኖታዊ እውቀት እንዲኖረው ከአሉባልታዎች እንዲጠበቅና የአክራሪነት አመለካከትና ተግባር የሚታገል አቅም ሆኖ እንዲደራጅ መደገፍ ያስፈልጋል። ተጠሪነታቸውን በየራሳቸው ሃይማኖት ተቋም በማድረግ ህገመንግስታዊ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆኑ መደገፍ ይቻላል። ” ሲል ይተነትናል።

” እያንዳንዱ የሃይማኖትና የእምነት ተቋም መሪዎች ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ከህገመንግስታዊ ስርአቱ ጋር የሚጋጩ እንዳልሆኑና ከዚህ ወጣ የሚል አካል ሲኖር በአባታዊ ምክር የመመለስና የማስታገስ፣ የማይታረም ከሆነም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የህግ የበላይነትን ማስከበት ” እንደሚጠበቅባቸው የሚገልጸው ሰነዱ፣ ” የሰባኪያን/ዳኢዎች ሚና የበለጠ ለማጎልበትና የተጠያቂነት ስርአት ለመትከል እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የራሱን መምህራን የሚለይበትን የመታውቂያ ስርአት ሊያበጅና በዚህም የክትትል ስራ እንዲሰሩ መደገፍ ይቻላል” ይላል።

ከሁሉም በላይ የአክራሪነት ተጋላጭነት እየመጣ ያለው የሃይማኖታዊ እውቀት ክፍተት የሚሞላ የተማረ የሰው ሃይል እየተሟጠጠ በመሄዱ” በመሆኑ ፣ በአጫጭር ኮርሶችም ይሁን በመደበኛ ፕሮግራም ከሰርትፍኬት አንስቶ እስከ ዲግሪ ፕሮግራሞች የሚያስተምር የትምህርት ተቋም አስፈላጊ ይሆናል” ብሎአል።