ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች ድብቅ መሳሪያ ተክለው ከውጪ አገር የሚደውሉ የስልክ ጥሪዎችን በራሳቸው መሣርያዎች በመቀበልና ለደንበኞች በማስተላለፍ በሕግ የተከለከለ የስልክ አገልግሎት እየሰጡ ነው ሲል ኢትዮ ቴሌኮም አጋለጠ።
በ1995 ዓመተ ምህረት ሟቹ ኢያሱ በርሄ እና ሌሎች ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ባስገቧቸው የቪሳት መሳሪያዎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሢሰጡ ተይዘው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።
ይሁንና ኮርፖሬሽኑ በግለሰቦቹ ምክንያት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንዳጣ ቢረጋገጥም፤በክሱ ምርመራ ሂደት ከቀድሞው የህወሀት ታጋይ ከ አርቲስት ኢያሱ በርሄ ጋር በመሆን የተጠቀሰውን ተግባር እየፈፀሙ ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አንዷ፦ ቀዳማይት እመቤት አዜብ መስፍን ሆነው በመገኘታቸው፤ ተከሳሾቹ በነፃ እንዲሰናበቱ መደረጉ በወቅቱ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች በስፋት ዘግበዋል::
ለተከሳሾቹ በነፃ መሰናበት በፍርድ ቤት በኩል የተጠቀሰው ምክንያትም፤የቀድሞው የ ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የደረሰበትን ኪሳራ በሚገባ ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ አልቻለም የሚል እንደሆነም አይዘነጋም።
ይህ ከሆነ ከዘጠኝ ዓመት በሁዋላ ነው ኢትዮ-ቴሌኮም ኢትዮጵያ ውስጥ በድብቅ መሳሪያ የተከሉ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች ህገ ወጥ የቴሌ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው።
ኢትዮ ቴሌኮም፦ ሱሉልታ በሚገኘው ሳተላይት ተቀብሎ ለደንበኞች ማስተላለፍ የነበረበትን የውጪ አገር ጥሪዎች፣ እነዚህ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች በውል ባልታወቀ ሥፍራዎች በተከሏቸው መሣርያዎች አማካይነት እየተቀበሉ በማስተናገድ ላይ እንደሆኑ ያጋለጡት፤ የኢትዮ ቴሌኮም አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ናቸው።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህ ሕገወጥ የስልክ አገልግሎት እየተካሄደ እንደሆነ ሊደርስበት የቻለውም፤ ከደንበኞች በደረሱት ጥቆማዎች እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል::
የተለያዩ ደንበኞች ከአሜሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ ሞባይላቸው በሚደወልላቸው ወቅት በሞባይላቸው ላይ የሚወጣው ቁጥር የውጪ ሳይሆን የአገር ውስጥ ሞባይል ቁጥር እንደሆነ ሀላፊው ለኢትዮ ቴሌኮም አስታውቀዋል::
የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ በበኩላቸው፤ የተጠቀሰውን ጉዳይ አስመልክቶ መስሪያ ቤታቸው ጥቆማ እንደደረሰው አረጋግጠዋል::
ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳዩን በጥንቃቄ በመመርመር ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አብዱራሂም፣ የተባሉት መሣርያዎች የተተከሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በጐረቤት አገሮች ሊሆን እንደሚችልም ጥርጣሬያቸውን ተናግረዋል::
ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎችን በሳተላይት ተቀብሎ ለደንበኞች የሚያስተላልፈው ኢትዮ ቴሌኮም ሲሆን፣ ለዚህም አገልግሎት የውጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች በየዓመቱ መጨረሻ ይከፍሉታል::
በአንፃራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለዚህ አገልግሎት የምታስከፍለው ክፍያ ከፍ ያለ በመሆኑ፣ አቅሙ እና በአመዛኙ ከባለስልጣናት ጋር ንክኪ ግለሰቦች የራሳቸውን መሣርያዎች በመትከል ተመሳሳይ አገልግሎት በአነስተኛ ክፍያ በመስጠት የቴሌን ሥራ እንደሚሰሩ ይነገራል።
በ አሁኑ ጊዜ የቴሌ ማኒጅመንት እና አመራር ሙሉ በሙሉ በህወሀት ጀነራሎች ቁጥጥር ውስጥ መውደቁን ያወሱ የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ፤ ድብቅ መሳሪያ በመትከል የቴሌ አገልግሎት በመስጠቱ ህገ ወጥ አሠራር ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሙሰኞቹ ህወሀቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም ብለዋል።
“ከታች እስከ ላይ፤ ከተራ የስልክ ኦፕሬተር እስከ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ቴሌ በህወሀት ሰዎች ስር ወድቋል። በድርጅቱ ውስጥ ባሉ የሀላፊነት መዋቅሮች በሙሉ የተቀመጡት ህወሀቶች ናቸው። ጥሪዎችን የሚጠልፉት፣የሚቆርጡት፣የሚቀጥሉት፣የሚፈቅዱት፣የሚከለክሉት…እነሱ ናቸው።እነሱ ሳያውቁት የሚደረግ አንድም ግንኙነት የለም” ያሉት እኚሁ ግለሰብ፤ “ቀደም ሲል ይህን ነገር ሲፈፅሙ የነበሩት እነ ወይዘሮ አዜብ እንደነበሩ ልንረሳው አይገባም” ብለዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide