ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነቱን ወሰደች

ጥር ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ለመጪው አንድ ዓመት የ አፍሪካ ህብረትን በሊቀ-መንበርነትን እንዲመሩ ተመረጡ።

እሁድ አዲስ አበባ  በተካሄደው የ አፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የመሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ከቤንን መረከቧን የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ዘገቧል።

ይህን ታላቅ ድርጅት ለመጪው አንድ ዓመት እንድመራ በመመረጤ ጥልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል-አቶ ሀይለማርያም።

<<ሹመቱንም የምቀበለው በታላቅ አክብሮትን የደስታ ስሜት ነው>> ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያ የ አፍሪካ ህብረትን የ አንድ ዓመት የሊቀመንበርነት ጊዜ ከቤኒን ለመረከብ ፍላጎቷን ያሳየችው ከሳምንታት በፊት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በሰጠችው መግለጫ ነው።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ << የሊቀ-መንበርነቱ ተረኛ ኢትዮጵያ ነች> በማለት ቀደም ብለው የሰጡት መግለጫ፤በህብረቱ አባል አገራት ዘንድ-<<የህብረቱን ፕሮቶኮል ያላከበረ>>ነው የሚል ትችት ማስከተሉ ይታወሳል።

ትችት የሰነዘሩት አባል አገራት ፤ኢትዮጵያ ሊቀመንበርነቱን  ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳየችው ተራዋ ሆኖ ሳይሆን ህብረቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የሚያከብርበት ስለሆነ ሹመቱ ከዚያ ጋር እንዲገጣጠምላት በማሰብ ነው ባይ ናቸው