ኢሳት (ሃምሌ 28 ፥ 2008)
በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ የለም ሲል የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ከተረጋገጠ የማስተካከያ እርምጃን እንደሚወስድ ለግብፅ መንግስት ማረጋገጫ ሰጠ።
የውሃ ሃብት ሚንስትሩ አቶ ሞቱማ መካሳ ሃገራቸው ግድቡ በተለይ በግብፅና ሱዳን ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ መኖሩ በባለሙያዎች ከተረጋገጠ ተፅዕኖውን ለመቀነስ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ለግብጹ አክባር አልዩም ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የግድቡ ግንባታ ከአራት አመት በፊት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በግድቡ ላይ ምንም አይነት ማስተካከያ እንደማይደረግ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ግድቡ የሚያመጣው ተጽዕኖ እንደማይኖር በመረጋገጡ ምክንያት ኢትዮጵያ ግንባታውን ለሰከንድም ቢሆን ማዘግየት እንደማትፈልግ በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ መግለጹ የሚታወቅ ነው።
ይሁንና የውሃ ሃብት ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መካሳ ሃገራቸው ከግብፅና ሱዳን መንግስታት በመተባበር ግድቡ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ዝግጁ መሆናን ለመጀመሪያ ጊዜ ማረጋገጫን እንዲሰጡ ለመረዳት ተችሏል።
ሁለቱ ሃገራት ሁለት የፋይናንስ ኩባንያዎችን በመቅጠር ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት በተለይ በግብፅ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማስጠናት መወሰናቸው ይታወሳል።