ኢሳት (ሚያዚያ 30 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት የተቃማዊ ፓርቲ አባላትን፣ ነጻ የመገናኛ ብዙሃንና፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ። በቅርቡ ጊዜ በመንግስት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ የተድረገውን ሪፖርት ማረጋገጥም መቀበልም እንዳልቻሉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን የጎበኙት ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አል ሁሴን በተለይ ከዶቼ ዌሌ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፣ በኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት መርማሪ ቡድን ምርመራ እንዲያደርግ ግፊት ማድረቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ አሁንም ምርመራ ለማድረግ የቀረበው ጥሪ ተቀባይነት አላገኘም።
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግስት በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ በገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ምርመራን አስመልክቶ የቀረበለትን የገለልተኛ ምርመራ ጥሪ ሳይቀበለው መቅረቱ የሚታወስ ነው።
ለጆቼ ዌሌ ራዲዮ ጣቢያ ኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ዛይድ ራድ አል ሁሴ፣ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚጠበቅባት አስምረዋል። ኢትዮጵያ በሲቪልና በፖለቲካው መስክ መስራት ይኖርባታል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሯ መክፈት እንዳለባት ያሰመሩት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ፣ በመንግስት የሚታገዘው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሊኖረው ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት መርማሪ ኮሚሽንን ህዝባዊ ተቃውሞዎች በተካሄዱባቸው ቦታዎች የራሱን ቡድን ለመላክ የኢትዮጵያን መንግስት ፈቃድ በድጋሚ ጠይቀዋል። ቡድናቸው በቦታው ተገኝቶ ምን እንደተከሰተ ማጣራት ይፈልጋል ሲሉ ዛይድ ራድ አል ሁሴን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት የሚታገዘው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው አመት ከሰኔ እስከ ጥቅምት ድረስት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በተካሄዱባቸው አካባቢዎች 669 ሰዎች መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም መታሰራቸው ተመልክቷል። ሆኖም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ መንግስት የወሰደው የሃይል ዕርምጃ ተመጣጣኝ ነው ሲል መግለጹ አይዘነጋም።
ለኢትዮጵያ ባለስልጣናትም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅት የቀረበውን ሪፖርት መቀበልም ሆነ ትክክለኛነቱ ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ገልጸው፣ እነሱ ያቀረቡትን ሪፖርት ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልቻልኩም ብለዋል። ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት መርማሪ ቡድን ወደ አካባቢዎቹ በመንቀሳቀስ ምርመራውን ማቅረብ ያለበት ሲሉ ተደምጠዋል።
ኮሚሽነሩ በሚቀጥለው ጥር ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድኑን እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንደሚፈቅድ ምኞቻተቸው መሆኑን ተናግረዋል።