ኢትዮጵያ የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት በከፍተኛ ሁኔታ ከተመዘገበባቸው አገሮች አንዷ መሆኗ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ይፋ አደረገ

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008)

ኢትዮጵያ የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት በከፍተኛ ሁኔታ ከተመዘገበባቸው 34 የአፍሪካ ሃገራት መካከል በ22ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አንድ አለም አቀፍ ተቋም ይፋ አደረገ።

በሴኔጋል መዲና ዳካር አመታዊ ሪፖርቱን ያቀረበው የአፍሪካ የሂሳብ ሳይንስ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ አለመረጋጋት ዝቅተኛ ክፍያና የከፍተኛ ትምህርት እድሎች አለመኖር ችግሩን እያባባሱት እንደሚገኙ መግለጹን ሜይል ኤንድ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።

አፍሪካ ካላት አጠቃላት የሃኪሞችና የምህንድስና ባለሙያዎች በላይ አፍሪካውያን ባለሙያዎች በአፍሪካ እንደሚገኙ ያስታወቁት ድርጅቱ የአህጉሪቱ መሪዎች የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰቱን ለመቀነስ አመርቂ እርመጃ አለመወሰዳቸውንም አመልክቷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት እየተደረገ ያለው የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰትም የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከመጉዳቱ በተጨማሪ ሃገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ጎድቶት እንደሚገኝም ተቋሙ ገልጿል።

ሩዋንዳ ከአፍሪካ ሃገራት መካከል የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰትን ለመቀነስ አመርቂ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን፣ ዛምቢያና ጋና የተማረ የሰው ሃይላቸውን ጠብቀው ለማቆየት እንደቻሉ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ቡሩንዲና ዚምባብዌ ከአፍሪካ የተማረ የሰው ሃይልን ከሚያጡ ሃገራት መካከል ግንባር ቀደም ሆነው ተፈርጀዋል። ስዊዘርላንድ፣ አሜሪካና፣ ኳታር ደግሞ ባለሙያዎቻቸውን በመጠበቅ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ችለዋል።

ሞሪታኒያ፣ ጊኒ፣ ቻድ፣ ዩጋንዳ፣ እና ካሜሮን ከኢትዮጵያ ተርታ የተማረ የሰው ሃይላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያጡ ሃገራት ተርታ የተቀመጡ ሲሆን፣ ሃገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ መሆኑም ታውቋል።

በ140 ሃገራት ላይ በተደረገ የተወዳዳሪነት ጥናትም ኢትዮጵያ በ109ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የአለም አቀፉ የተወዳዳሪነት ጠቋሚ መረጃ አመልክቷል።

ሃገራት በአለም ተወዳዳሪነት ያላቸው ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ባላቸው እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ  እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።