ሰኔ ፲፭( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየዓመቱ በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ በመፍረስ እና ለመፍረስ አደጋ ያንዣበባቸው አገራትን በሚያጠናው ፍራጃይል ስቴት ኢንዴክስ(Fragile States Index) ተቋም ጥናት መሰረትኢትዮጵያ አደጋ ካንዣበበባቸው አገራት ተርታ ተመደበች።
የሟሸሹ አገራት ተርታን አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በቀዳሚነት ስትመራ ፊንላንድ አሁንም የሰላም ዋስትና ያላት የመጀመሪያዋ አገር ሆና ተመርጣለች።ሌላዋ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ኢትዮጵያ፣ ሜክሲኮ እና ቱርክ ከ2016 እ.ኤ.አ. ጀምሮ እንደ አገር ለመቀጠል አደጋ የተጋረጠባቸው የዓለማችን አገራት ተብለዋል።
ካደጉ አገራት ደግሞ አሜሪካ እና እንግሊዝ ከነበራቸው ደረጃ አሽቆልቁለው የከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጥናቱ ይተነትናል። የመፍረስ አደጋ ያንዣበባቸውን አገራት የሚያጠናው ፍራጃይል ስቴት ኢንዴክስ ላለፉት 13 ዓመታት በተከታታይ ዓመታዊ የጥናት ሪፖርቱን ሲያቀርብ ቆይቷል።
በዘንድሮው ዓመት በ178 የዓለማችን አገራት ላይ በተደረገው ጥናት የሕዝቦች ብሶት እያደገ መምጣትና መንግስታት የሚወስዷቸው የኃይል እርምጃዎች ለግጭቶች መባባስ ከፍተኛውንድርሻ እንደሚወስዱ ተመልክቷል።
ተቋሙ፣ በአገራቱ ያለውን የጸጥታ እና የግጭት አፈታት ሁኔታ፣ የእድገት ደረጃቸውንና የሀገራቱን የፖሊሲ ቀረጻ ግብአቶችን በጥልቀት በማጥናት ደረጃውን እንደሚያወጣ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አስመልክቶ ድርጅቱ ባቀረበው ሪፖርት ካለፈው ዓመት ከተቀሰቀሰውሕዝባዊ እንቢተኝነት ወዲህ አገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ተስኗታል ብሏል። በተለይ በኦሮሚያ እናአማራ ክልሎች የተነሳው ሕዝባዊ ማዕበል ገዥውን ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ እስከማስገደድ መድረሱን ጠቅሶ፤አስቸኳይ የጊዜ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች በግፍእንደተገደሉ አትቷል። ገዥው ፓርቲ አዋጁን የዜጎችን መብት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንን እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን ለማፈኛነትም ተጠቅሞበታል ብሏል።በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ400 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። የኢትዮጵያ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ሳይሻሻል ዘንድሮም እየከፋ መምጣቱንም እና ለረዥም ግዜምእየተንከባለለ እንደሚቀጥል ጥናቱ ያብራራል። በሥጋት መጠን በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ ከነበረችበት 91.9 በመቶ 101.1 በመጨመር ቁልቁል በመሄድ ላይ መሆኗን የጥናት መለኪያመስፈርቱ ያሳያል።የተቋሙ ጥናት እንደሚለው፤ ከጸጥታና ሰብዓዊ መብት አፈናው በተጨማሪም ድርቁን ተከትሎ በተከሰተው ርሃብ ምክንያት የምግብ እጥረት መፈጠሩም፣ በአገሪቱ ሕልውናላይ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ፈጥሯል። በድርቁ ምክንያት የግጦሽ ሳር ፍለጋ በሚሰደዱ አርብቶ አደሮች መሃከልም ግጭቶች ተቀስቅሰው የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፋቸውን ጥናቱ አስፍሯል።ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ጋር በተያዘ የመሬት ቅርምቱን በመቃወም የተጀመረው ሕዛባዊ አመጽ በመላው አገሪቱ ለተስፋፋው ሕዝባዊ እንቢተኝነት መነሻ መሆኑንም የፍራጃይል ስቴት ኢንዴክስ ጥናትን በመጥቀስ ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።