ኢሳት (ሚያዚያ 24 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት የሃገሪቱን ገጽታ ሊያበላሽ ይችላል በሚል በመንግስት ችላ ተብሎ ቆይቷል የሚል ትችት በመቅረብ ላይ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ማከሰኞ ዘገበ።
በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ድርቅና ረሃብ አደጋ ተመልሳለች መባልን እንደማይፈልግ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አስነብቧል።
ይሁንና፣ ድርቁ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል እያደደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት ሲያደጉ መቆየታቸውን ጋዜጣው የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ ለማድረግ በዘገባው አስነብቧል። ባለፈው ሳምንት የተረጂዎች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 7.7 ሚሊዮን ማድረጉን መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋራ ባወጡት አዲስ ሪፖርት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
መንግስት የቁጥሩን መጨመር ከመግለፁ በፊት የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተመሳሳይ ቁጥርን አውጥቶ እንደነበር ሲዘግብ ቆይቷል።
ይሁንና መንግስት የተረጂዎችን ቁጥር እና እያደረሰ ያለውን ጉዳት ከመግለፅ ለወራት ያህል ተቆጥቦ ቆይቷል ሲሉ የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ትችት ማቅረብ መጀመራቸውን ከአለም አቀፍ ጋዜጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ተመሳሳይ ድርቅ ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች በተከሰተ ጊዜ መንግስት ለወራት ያህል ዝምታን መርጦ ቆይቷል ሲል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አውስቷል።
የአሜሪካው ፈጣን የምግብ አቅራቢ የሆነው ፒዛ ሃት (Pizza Hut) ባለፈው ሳምንት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ እንደሚከፈት ይፋ በተደረገበት ወቅት በሃገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በምግብ እጥረት የአካልና የጤና ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጋዜጣው በንጽጽር አቅርቧል።
በተለይ በሶማሌ ክልል ያጋጠመው የምግብ እጥረት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የአለም ምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች እየሰጠ ያለው የምግብ አቅርቦት በ80 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉም ታውሷል።
በክልሉ እየሰጠ ላለው አገልግሎት የ121 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት አጋጥሞት የሚገኘው ድርጅቱ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ በእጁ ያለው ገንዘብ እንደሚያልቅም ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የአለም ምግብ ተወካዮችን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስፍሯል። የድርጅቱ የአፍሪካ ቃል አቀባይ የሆኑት ቻሊስ ማክ-ደኑግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው በተለይም በሶማሌ ክልል ያጋጠመው የምግብ እጥረት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ለተረጂዎች እየሰጠ ያለው የምግብ እጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መንግስት 5.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ቢገልፁም ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ኣስካሁን ድረስ የተገኘው ድጋፍ ግን ከ150 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና የሶማሌ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ከፍተኛ አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑ ይታወቃል።