ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለት እስር ቤቶች ውስጥ ብቻ 401 የፖለቲካ እስረኞች እንደሚገኙ ተገለጸ

መጋቢት ፳፮ (ሃይ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት በፖለቲካ አመለካከቱ የታሰረ አንድም ሰው የለም ቢልም ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ  በሁለት እስር ቤቶች ውስጥ ብቻ 401 የፖለቲካ እስረኞች እንደሚገኙ ተገለጸ።

የተጠቀሰው የፖለቲካ እስረኞች አሀዝ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታሠሩትን ብቻ እንጂ፤ከዚያ በፊት ያለውን እንደማያካትትም ተመልክቷል።

ምንጮቹን በመጥቀስ ፍኖተ ነፃነት  እንደዘገበው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ የሀሰት ክስ የተመሰረተባቸው  401 እስረኞች የሚገኙት፤በቃሊቱና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ነው።

የጋዜጣው ምንጮች ከየማረሚያ ቤቱ የላኩት  ሰነድ እንደሚዘረዝረው፤ “በ36 የተለያዩ  ፋይሎች ክስ የተመሰረተባቸው   401 ፖለቲከኞች የኢህአዴግ ካድሬዎች፣ደህንነት፣ፖሊስና ዐቃቢ ህግ ባቀነባበሩባቸው  የፈጠራ ወንጀል የሀሰት ምስክር፤ በየማረሚያ ቤቱ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ።

ከነዚህ 401 ታሳሪዎች መካከል፤ “የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/፣የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/፣የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ/ኦህኮ/፣የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ኦፌዴን/፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ /ኢብአፓ/፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ   ፓርቲ /መኢዴፓ/ አባላትና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ሰነዱ ያመለክታል።

 እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ምክንያት በተቀነባበረ የፈጠራ ወንጀል በግንቦት ሰባት፣በኦነግና በኦጋዴን ነፃ አውጪ አባልነት ስም ታስረው በመሰቃየት ላይ የሚገኙ እስረኞች መኖራቸውን ሰነዱ ያሳያል፡፡

 

የአቶ መለስ መንግስት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ  የፖለቲካ እስረኛ የለም በማለት በተደጋጋሚ ለማስተባበል ሲሞክር ይደመጣል።

ምርጫ 97 ትን ተከትሎ የቅንጂት አመራሮች፣ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበር አመራሮች ሢታሰሩ፤እንዲሁም በ 2000 ምርጫ ሰሞን የአንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር የነበሩት  ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ በታሰሩ ጊዜ አቶ መለስ በተደጋጋሚ፦ “ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም” ማለታቸው ይታወሳል።

ሆኖም፤እስረኞቹ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የላኩት ይህ ሰነድ፤ የታሳሪዎቹን ማንነት በዝርዝር የያዘ መሆኑ ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁለት እስር ቤቶች 401 የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ከታጎሩ፤ ኢህአዴግ ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ በጠቅላላ አገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች ያስገባቸው የፖለቲካ እስረኞች በስንት ሺህ ይቆጠሩ ይሆን?ሢሉ አንድ የጋዜጣው አንባቢ ጠይቀዋል።

ኢሳት ባለፈው አንድ አመት ብቻ በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ 400 የፖለቲካ እስረኞች ታስረው እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ሲገልጥ መቆየቱ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና በሀገሪቱ ውስጥ በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰትና የሕጋዊ ስርዓት መናጋት ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ መሄዱ እጅጉን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ገልጧል።

መድረክ  ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው የድርጅቱ አባላት የሆኑ ዜጐች  የፈለጉትን የፖለቲካ መስመር ደግፈው ያልፈለጉትን ተቃውመው በሰላም መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል።  ከመድረክ አባል ድርጅቶች መካከል የአረና እና የኦፌዴን አባላት ስቃይ እየደረሰባቸው ነው ብሎአል።
ድርጅቱ በሚንቀሳቀስበት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቄለሞ ወለጋ ዞን በሀዋ ገላንና በሀዋ ወለል ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ዜጎች “ሌቦች ናቸው፣ ቦዘኔዎች ናቸው” በማለት በፖሊስና በሚሊሺያ ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመወሰድ ከባድ ድብደባ እንደደረሰባቸው መረዳቱን ድርጅቱ ገልጦ ፤ በሀዋ ወለል ወረዳ መስራ ቀበሌ ሰንበቶ ወዬሳ፣ ይልቅ እስራኤል፣ ደገፉ ሲራጋ እና ወሰኑ ዲሳሳ የተባሉ ሰላማዊ ዜጐች በፖሊስ ጣቢያ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ ሰብአዊ ክብራቸውን በማዋረድ ኋላ ቀር በሆነ የቅጣት አፈፃፀም በህዝብ ፊት እና በገበያ ውስጥ መገረፋቸውን እንዲሁም በሀዋ ወረዳ ጉራቲ ወለል ቀበሌ ነዋሪ የሆነ ረጋሳ ቱቾ የካቲት ወር በቶጆ ወረዳ በፖሊስ ተይዞ በመደብደቡ ህየወቱ ማለፉን እና አስከሬኑም ተገቢው የህክምና ምርመራ ሳይደረግለት መቀበሩን ጠቅሷል። ግለሰቡን ያለምርመራ እንዲቀበር ያደረጉትን ወንጀል ለመሸፈን የተወሰደ እርምጃ መሆኑን የገለፀው ድርጅቱ፤ የተወሰደው የሕግ ጥሰት የፍትህ ስርዓት ላይ እምነት ያሳጣቸው የአቶ ረጋሳ ቶቾ ባለቤት ወይዘሮ ተመስጌ ለሙ በድርጊቱ ተበሳጭተው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ራሳቸውን በመስቀል ህይወታቸው በአሳዛኝ ሁኔታ አጥፍተዋል ብሎአል። ከዚህ በተጨማሪም ከሟች ረጋሳ ቱቾ ጋር በወቅቱ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የነበሩት ሰንበቶ ወዬሳ፣ ገመቹ ፈጠነ እና አማና ጨዋቃ የተባሉ ንፁሃን ዜጎች ከባድ ድብደባ ተፈፅሞባቸው በህክም ላይ እንደሚገኙ ገልጧል።

በቄለሞ ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በጐዳና ጨዋቃ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ላይ ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ መፈፀማቸውን፣ በደቡብ ክላላዊ መንግስት በሀላባ ልዩ ወረዳ የቀበሌ ባለስልጣናት የስልጣን መቀራመት ሽኩቻ ባስከተለው ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉ፣ በሀዲያ ዞን፣ በምስራቅ በዳዋቾ ወረዳ በቀበሌዎች አከላለል ጉዳይ ላይ በህዝቡ መካከል ስምምነት በመጥፋቱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት መድረሱን ድርጅቱ እንደደረሰበት አክሎ ገልጧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide